Tuesday, September 29, 2009

ዘፍናችሁ ቅበሩኝ

ሰውን ሰው አሳዶ-ቢያሳጣው መድረሻ
ጭንቅ ብርክ አስይዞ- ፍፁም መተንፈሻ
ሚሊዮኖች ቢያልቁ- በርሃብ በበሽታ
ጦርነት ቢመረጥ- በሰላሙ ፋንታ
….
መስማማት ተጠልቶ- መናቆር ቢሞገስ
ቅዱሱ ቢረክስ- ርኩሱም ቢቀደስ
ህግ የጉልበት ሆኖ-ፍትህም ተጠልፎ
አስታራቂ ጠፍቶ- ዳኝነት ተገፍፎ
መስገብገብ ህግ ሆኖ-ሙስና ተለምዶ
ቅጥፈት ተሞካሽቶ-እውነትም ተዋርዶ
ቀማኛን ሆነና - የሚሰማ ጆሮ
ቁብ የሚለው ጠፋ- የደሃን እሮሮ
እጥፍ ድርብ ሆነ- ስቆቃው ጨመረ
አይኔን እንባ ሞላው-ልቤ ተሰበረ።
አንገቴን ደፍቸ- መሬትን እየጫርኩ
መሞት እንደምሻ- ለአምላኬ እየነገርኩ
ጸሎቴ ተሰምቶ-አርጎ ሰማይ
ሞቴ ደረስልኝ- ይህን እንዳላይ።

ዛሬ መሄጃዬ- ተራዬ ነውና
ከየመንደራችሁ-በጠዋት ውጡና
ሸኙኝ ጨፍራችሁ- በዘፈን በዜማ
ሞትን መርጫለሁ ይህን ከምሰማ።

እናቴ አታልቅሽ- አይመታ ደረት
አባቴም አትተክዝ- እኔስ ልሂድበት
ትቸው የምሄደው- የምተወው ዓለም
ከሞት የባሰ እንጅ- የተሻለ አይደለም።

ፅድቅና ኩነኔ- ቢኖርም ባይኖርም
ለእኔ እዚህ መኖሬ- ከሞት አይሻልም
እኔስ በፈጠረኝ- እመካለሁና
ህይወት ይኖረኛል- ገነት እንደገና ።

አልያም…
ሚካኤል ከበሩ- ባይቀበለኝም
አቡዬን ተክልዬን- ላያቸው ባልችልም
ገነት መግባት ቀርቶ- ገሃነም ብወርድም
ቁርጥ ያጠግባልና- አማረ አላማረም
ከመሞት መኖርን- በፍፁም አልመርጥም

የዚህ ዓለም ኑሮ- የአምሳያዬ ግፉ
ሞትን አስመረጠኝ- ተሽሎኝ ማረፉ።

እናም አታልቅሱ- አልሥማ ዋይ ዋይታ
በምትኩ አሳዩኝ- ዘፈንና እስክስታ
ክራር ጽናጽሉ-ከበሮው ይመታ
በገና ይደርደር-አስራ ሁለት ተርታ
ይነፋ ዋሽንቱ- ሳክስፎን እምቢልታ
ወንዶቹ በሆታ- ሴቶቹ በእልልታ
የዛሬን--የዛሬን- እኔን ደስ እንዲለኝ
ማልቀሱን ተውና -ዘፍናችሁ ቅበሩኝ።

ዳግማዊ ዳዊት
መስከረም 2002 ዓ.ም.
ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: