Friday, September 11, 2009

ጥጃ- ለዘመን መለወጫ

በግንባሩ ወግቶ- ቢያጠቃኝ በርግጫ
ቢላ ቢላዋ አለኝ- ለዚህ ክፉ ጥጃ።
ዘመን ተለውጦ-ዘመኑ እስኪተካ

“ይወርዳል… ይለቃል”- ወሬ እንዳልተቦካ
ይኸ ጥጃ እምቢ አለ- አልሄድ ብሏል ለካ!
ሰፈሩን አመሰው-አጉል ተፈራግጦ
ሰው ግራ ገባው- በጭንቀት ተውጦ
እረኛ አይመልሰው-አዳኝ አያድነው
ሰውን እየጎዳ-ከአካል እያወጣው
ለህልፈት ሲዳርግ- እፎይታ ሲያሳጣ
ኑሮን ክፉ ትርኢት- ሲያበዛበት ጣጣ
ምን ጉድ ሆነ እና ነው- ይህ የሰፈር ጥጃ
ጀግና የለም እንዴ-የሚያውቅ ጠመንጃ።


እናንት አድርባዮች- ዘመን ስትለውጡ
ከዚህ ክፉ ጥጃ- አብራችሁ አትውጡ
ብትቀሩ ይሻላል- እናንተስ አትምጡ።
እናንት ወገኖቼ- ከብት የምታረቡ
ይህን ክፉ ጥጃ- ከእናንተ አትደንቡ
እናንተ ተለዩ- ወደተራራው
ያ ክፉ ጥጃ ነው- ገደል የሚያምረው።
አጨደው ሰርዶውን- የሰፈሩን ሙጃ
ምላሱ መርዝ አለው- እግሩ የጦር ሳንጃ
ረሃብ ላይ ጣለው-ፍየልና በጉን
አጉልኛ ጠባት- ያች ደግ እናቱን
ጀግና ምነው ጠፋ- የሚያድን ላሚቱን።

ቄራ ሰራተኞች-በግ የምታግዙ
እስኪ በዚህ ዓመት-ይህን ጥጃ ግዙ
ገበያ ውሰዱት-ለዚህ አዲስ ዓመት አራጅ
እንዲወስደው- ሁሉን የሚያውቅበት
አቅርበው ለሽያጭ-ሲራራው ነጋዴ
በሰላም ልተኛ-ይረፍልኝ ሆዴ።
ከሰሜን ከምስራቅ- ከምዕራብ ከደቡብ
ተሰባሰብና- ሁሉም ያገሬ ህዝብ
ደስ ብሎን እንድንውል- ዘመን መለወጫ
ጨፌ ጎዝጉዛችሁ- ቄጠማ ወይ ሙጃ
አንገቱ ላይ አርጉ- ቢላዋ ወይ ሳንጃ
ገላግሉን በአንድዬ- ከዚህ ክፉ ጥጃ።


ዳግማዊ ዳዊት
መስከረም 2002 ዓ.ም.

No comments: