Saturday, September 19, 2009

የሶፋው ጄነራል

ከሰዓት በኋላ- አንድ እሁድ በበቴ
ቡና እየተፈላ- መጥተው ጎረበቴ
ወሬው ደርቶ ሳለ- ቡናው እየፈላ
ሃሳብ ስንጋራ- በተራ በተራ
የአገር ነገር መጣ- ወሬው ተጀመረ
እንደ አዲስ ጀመርነው- ልክ እንዳልነበረ።

“ይህ አገር አስገንጣይ- ይኸ ዘረ-ባንዳ
የአገር ጥቅምን ጎድቶ-ያደረ ለባዳ
በጎሳ ከፋፍሎ- ህዝብን ያናከሰ
አሁንስ መውደቂያው- መሄጃው ደረስ
ሸክ ሁሴን እንዳሉት- እንደተነበዩት
ብን ብሎ ይጠፋል- መቸም አይሰነብት።”

ብዬ ሳስተጋባ- እንድተለመደው
የወያኔን መንግስት ልንጠው- ልንደው
እኝህ ጎረቤቴ- እኝህ አባ ጎንጥ
በትዝብት አይተውኝ- ዘወር አርገው የጎሪጥ

“ኤድያ ..
ይህን ስትናገር- እኔም ሳዳምጥህ
ሴት ልጅህ ተወልዳ- ኮሌጅ ገባችልህ
ህፃን ልጇን ወልዳ- አያት አረገችህ
አንድም አትዋጋ- ወይ አርፈህ አትተኛ
ወይ ጸሎት አታደርግ- ለላይኛው ዳኛ
የያዘህ ይመስል- አስለፍልፍ መጋኛ
ሃያ ዓመት አለፈህ- ይህን ስታወራ
ሃገር ነፃ አትሆን- በባዶ ፉከራ።”

ብለው ሲጨርሱ- ዶ/ር ቀጠል አርገው
መናገር ጀመሩ- ጉሮሮን ጠራርገው
“እንደዚህ ዓይነቱ- የሁከት ዘመቻ
አርገው አይቁጠሩት- ችግር ለኛ ብቻ
የዓለሙ ኃያላን- የዚህ ምድር ጌታ
በታሪክ አልፈዋል- ልክ በኛ ቦታ
ዋናው ቁም ነገሩ- ማስተዋል ያለብን
ቁብ የሌለው መሪ- በህዝብ የሚጨክን
ትቶ እንዳያልፍ ነው- የታሪክ ጠባሳ
ለሚመጣው ትውልድ -የሚተርፍ አበሳ
አባቶች ነገስታት- የምንወዳቸው
አገር ወዳዶቹ- ታሪክ ዘካሪያቸው
እነደመልካም ሁሉ- መጥፎ ተግባራቸው
እሳቱ ተረፈን- ይኸው ልጆቻቸው
ትናንት ጎበናን -ምንልይክን ሲሉ
እግዚኦ ሲባልበት-ቦሩ ሜዳ ሁሉ
ራስ ሚካኤል ላይ-ሲፈስ ፀበሉ
ነገሥ “መለስ” ሲባል- ልጆች ምን ይላሉ?
ስለዚህ እንበርታ- የእኛን እንወጣ
እኛው በእኛ እንፍታው-ያለብንን ጣጣ
ችግሩን አያውቀው- ባዕድ ብናመጣ።”

ከመቀመጫየ- ተቁነጠነጥኩና
እናገር ጀመረ- ይኸው እንደገና።
“ይልቅስ ህዝባችን- ምንድን ነው የነካው
እስከዛሬ ድረስ- ዝም ብሎ የሚያየው?
አሁን ቃል እንግባ- ዛሬስ እንማማል
ባባቶች በእናቶች- ባባ ጎንጥ መሃል
ይህን አረመኔ- ይኸ ዲያቢሎስ
ዝም እንዴት ተባለ- እስካሁን ድረስ?
አዛውንት የገፋ- ህፃን የገደለ
አገር የበተነ- ደሃ የበደለ
ያከትማል ዘንድሮ- “ይለያል ዘንድሮ”
ያገር ገንጣዩ ልክ- “የወያኔው ኑሮ”
ተነሱ እንነሳ- እንዝመት ሁላችን
ከመለስ አገዛዝ -ትፅዳ ሀገራችን።”

ዘራፍ አልኩኝ እኔ- እንደተለመደው
የወያኔን መንግስት- ልንጠው ልንደው።

ያጤኑት ሳይመስለኝ-ይህን ፉክራዬን
ትናንትና ዛሬ- ያነበነብኩትን
ከሶፋየ ሳልርቅ- የማስተጋባውን
እማሆይ እናቴ- ሰልችቷቸው ኖሮ
ያሰሙ ቀጠሉ- ወቀሳና ሮሮ።
“አንተ ስትወለድ- ጾታ ሲጠይቁኝ
“ሴት” አለማለቴ- አሁን ነው የቆጨኝ
እንደ ቁጡ ሴቶች- ወገብክን ባትይዝም
መለፍለፍ ስትጀምር- ጭራሹን አታንስም
ሁሌ እዚህ ሶፋ ላይ- እግርህ ተዘርግቶ
ሰው ወሬ ሲጀምር- ከዚህ ሳሎን ገብቶ
የምትለፈልፈው- የምትፎክረውን
በነጋ በመሸ- ያነበነብከውን
ተንትኘ እናዳልነግርህ- አንድ በአንድ ሁሉንም
ዛሬ ይቅርና -ነገ አልጨርሰውም
እንዲያው ባይነገር- ወሬው ባይቦካ
የኔ ልጅ ጦረኛው- ሸፍቶ አማሪካ
ገዳይ ጦብያ ምድር- መሃል መንዝ ጫካ።”

ከት ብሎ ሳቀና- የሃያ ዓመት ጓዴ
ያምሰው ጀመረ- ያለውን በሆዴ
“እማማን ይስማልን- እግዜር ይባርክልን
ለዚህ ለወንድሜ- ልኩን ነገሩልን
እኮ ዘራፍ ማለት- ሽህ ማይል ርቆ
ጠላት እስኪሳለቅ- የራቀ ልብ አውቆ
አፍህ አላረፈ -ወይ ውጊያን አልጀመርክ
አለህ ከዚህ ሶፋ- “ዘራፍ ዘራፍ” እንዳልክ
የሶፋው ጄነራል- የስታርባክሱ ማርሻል
ከአንተ ዘራፍ ማለት- ዝም ያለ ሰው ይሻል
ወይ ደፍረህ ግባበት- ከመንዝ ተራራ
ገስግስ ወደ ሶማ- ዝመት ወደ አስመራ
በድል እንድትፎከር- እኛም እንድንኮራ።”

ይኸ ጓደኛዬ- የልብ አዋቂው
እውነትነት አለው -የተናገረው
ሶፋ ላይ ስፎከር- ሃያ አመት ሆነው
ፉከራ ብቻ ነው- እርሱም የሰማው
“የሶፋ ጄነራል”- እርሱም ሲያንሰኝ ነው
መቸ ይሆን ቃሌን ተግብሬ እማየው?


ዳግማዊ ዳዊት
መስከረም 2002 ዓ.ም.
Ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: