Wednesday, February 10, 2010

በረዶ (ኩችዬ)

ወዳጄ ልጅ አበራ! ሲፈራ-ሲቸር ያደረ መንፈሴን እንደምንም አነቃቃሁና ቀያችን የተከመረውን በረዶ ለመዛቅ ጧቱ ላይ ብቅ ብዬ ነበር -“ላይቀርልኝ ዕዳ!” ተብሎ የለ። ታዲያ ያልጠበቅሁት ነገር ገጠመኝ። ባወራረድ ውበቱና በነጠረ ንጣቱ ትናንት ሲያማልለኝና እንደመፈላሰፍም ሲያደርገኝ የነበረ ገራ-ገር በረዶ ዛሬ ፍጹም ጠባዩን ቀይሮ፤ እብሪተኛ “በላ ልበልሃ!” የሚል ጉድ ሆኖ አገኘሁት።
መቼም ዳጎስ ያለ ቁርስ ጎርሶና ትከሻውን ቼብ-ቼብ ተደርጎ የወጣ ወንድ የልብ ሳያደርስ አይመለስምና ወርደ-ሰፊ አካፋየን እያውልለበለብሁና ውርድ ከርሱ እንደሚሆን እያስጠነቀቅሁ በረዶ ላይ ጦርነት ከፈትሁ። አጀማመሬን በጣሙን ወደድሁት። በዚህ አያያዝ በራሴ ቀዬ ላይ የሚደነፋው ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ያሉ መበለት ደጃፍ የተከመረውም እንደማይተርፈኝ አረጋገጥሁ። የልብ ልብ ተሰማኝና አካፋውን ካፍ-እስከገደፉ እየሞላሁ አቶ በረዶን በትከሻየ ላይ እያሻገርሁ አሺቀነጥረው ጀመር።
እንተዬ! በ17 ዲግሪ ፋራናይት ሰው ያልበዋል እንዴ? ደግሞ ትንፋሺ ቁርጥ-ቁርጥን ምን አመጣው? እስቲ ትንሺ አረፍ ልበል አልኩና አካፋዬ ላይ ደገፍ እንዳልሁ ሀሳብ አነጎደኝ። ያ ያዲሳባው ዘበኛችን አያልነህ ፊቴ ላይ ድቅን አለ። አይ ግቢ ሲያሳምር! አይ መኪና ሲወለውል! የወዳጄ የመንግሥቱ ለማ “ባሻ አሸብር” ያገር ናፍቆት መነሻውና ሰበቡ ከምንጊዜም በበለጠ ውስጤ ገባ … “አወይ አዲሳባ ወይ አራዳ ሆይ፤ አገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ?!”
ጀመርኩ ደግሞ መዛቄን። ከፊቴ የተደቀነውንና ከኋላየ ያጠራሁትን ማነጻጸርም ዳዳኝ፤ ግን ውጤቱን ፈርቼ ተውሁት። “ደሞ ይሄ አካፋ ምን ነካው? ቅድም ካፍ-እስከገደፉ ይሞላ አልነበረም እንዴ? ያ ትከሻዬ አካባቢ ዞሮ የነበረው ሥር ሊያገረሺበት ፈለገ እንዴ ደሞ?”
እንዲህ ያካፋውን ስነፈትና የትከሻየን ልግመት በመታዘብ ላይ እንዳለሁ ነው ከመበለቷ ቤት አቅጣጫ “ርርርርርርር!” የሚል የሞተር ድምጽ ሰምቼ ዞር ያልሁት። እመቤቲቱ በረዶ መንፊያ መንኮራኩራቸው ላይ ቂጢጥ ብለው ቀያቸው ላይ በድፍረት የተጋረጠውን በረዶ የመነጥሩታል። እጃቸውን አውለበለቡልኝ። እኔም አውለበለብሁላቸው።
“አይ ተወው፤ የዘድሮው በረዶ ባካፋ የሚሞከር አይደለም! አንዳፍታ ጠብቀኝ እረዳሀለሁ!” አሉ ድምጻቸውን ከሞተሩ ድምጽ በላይ ከፍ አድርገው።
“ቀድሞውንም አውቄዋለሁ! የዘንድሮው በረዶ ልዩ ስለሆነ እንጂ የኔም የትከሻየም ያካፋውም መዳከም አይደለም” አልኩ ለራሴ።
“ኸረ ግዴለም ደህና ይዣለሁ!” አልኳቸው የሚያለከልክና የሚያሳጣ ድምጼን መደበቅ እያቃተኝ።
አባባሌ ከላይ እስከታች የመግደርደር ስሜት እንደተጻፈበት ያነበቡት እሜቲቴ መልስ እንኳ አልሰጡኝም። የራሳቸውን ቀዬ ከምኔ ፉት እንዳሉት ሳላውቅ መንኮራክራቸውን እያውተረተሩ ከች አሉ። በራሳቸውም ይችን መንኮራኩር ለመግዛት ባደረጉት ውሳኔም የቱን ያህል ኩራት እንዳደረባቸው መላ ፊታቸው ላይ ተጽፏል። እንኳንስ እኔ በረዶውም ከምሬት ጋር እንዳነበበው ታወቀኝ።
“ርርርር!” ከላይ እታች ተመላለሱበት። ጠላትህ ብን ይበል ያ ሲያሾፍብኝ ያረፈደ በረዶ ባንድ አፍታ ብን ብሎ ጠፋ። ካሁን ወዲያ በረዶ እሜቱቱም እኔም ቤት የሚደርስ አይመስለኝም። ካልቸገረው በቀር እኛ ሰፈር ዝር አይልም - ውርድ ከርሱ ነው ‘ሚሆነው!

--------------------------------------------------------------------------------

ኩችዬ

February 7, 2010

www.kuchiye.blogspot.com

No comments: