Wednesday, February 10, 2010

የመጪው ምርጫ ቧልትና ቁምነገር (ይኸይስ ሞረዳ)

ይኸይስ ሞረዳ - ከአዲስ አበባ

yihemore@gmail.com

እንደመንደርደሪያ
በኪነ ጥበብ ዓለም ቧልታይ ተውኔት (Farce) የሚባል የኮሜዲ ዘውግ አለ። የቧልታይ ተውኔት ዋና ተግባር የተጋነኑና በእውኑ ዓለም ከምናያቸው ሁነቶች ወጣ ያሉ፣ ከዕለት ተዕለት የኑሯችን ገጠመኞች የራቁ ጉዳዮችን ይሁነኝ ብሎ (deliberately) በመከሰት ተመልካችን ወይም አድማጭን ማሳቅ፣ ማዝናናትና ማስደሰት ነው። የኮሜዲ ዘር በመሆኑም ፍጻሜው በደስታ የሚደመደም ታሪክ ያለው ተውኔት ወይም ድራማ ነው። አድማጭም ሆነ ተመልካች ብዙ ቁምነገር የሚገበይበት አይደለም- ምንም እንኳ ሳቅና መዝናናት በራሱ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር ቢሆንም።

የደላው ሕብረተሰብ በቧልታይ ተውኔት የፈጠራ ጥበቡን ከፍታ ይጨምርበታል፣ ይዝናናበታል፣ ይደሰትበታል። እንደኛ ያለ በብዙ ማሕበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ድቀት ውስጥ እየማቀቀ ያለ ሕብረተሰብ ደግሞ ላፍታም ቢሆን ከውጥንቅጡ ፣ ከትብትብ ችግሩ፣ ከቁም ሞቱ ፋታ ሊያገኝበትና ሳያሰልስ ከሚላተመው የኑሮ ጣጣው ሊሸሽበት ይሞክራል። ቢያንስ እስከተውኔቱ ፍጻሜ ዘና ይል ዘንድ ያደርገዋልና ቧልት አይኑር አይባልም።

አለቦታው፣ አለሰገባው የገባ ቧልት
ቧልት በቦታው ሲሆን መልካም ነው። ዘና ያደርጋል። የተቸገርነው አለቦታው እየገባብን ነው። የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ጎስቋላ ኑሮ እና የአገራችንን የወደፊት ዕጣ በሚወስኑ ማሕበረ-ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥቂቶች የደላቸው ምርጫ የሚባል ቧልታይ ተውኔት እንደገና ወደመድረክ ይዘው ብቅ ሲሉ የመከራ ዘመናችን ያበቃ ዘንድ ከምር እንታገላለን የሚሉ ሃይሎች በዚህ የፌዝ ድግስ እንደተዋናይም ሆነ እንደታዳሚ ሲሳተፉ ቧልት ያለቦታው ገባ ያሰኛል። ለኢትዮጵያዊነት በሚያሳየው ንቀት፣ እንደሕዝብ ማንነታችንን ለሚያፀኑ እሴቶቻችን መሸርሸርና መጥፋት በሚሸርበው ሴራ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብራችንን ለማዋረድ በሚወርደው ቆላና በሚወጣው ደጋ ተወዳዳሪ ላላገኘንለት መሰሪ ሥርአት ቀኝ እጅ ማዋስ እንዳይሆንም እሰጋለሁ። ስለዚህ ድራማው እንደተመልካች ያሳዝነናል እንጅ አያዝናናንም። ምክንያቱም ቧልቱ ከፈጠራ ምናብ የተቀዳ የጥበብ ሥራ ሳይሆን በኛው በጎስቋላዎቹ ዜጎች ዕውናዊ መከራ ላይ የሚሳለቅ ትርዒት በመሆኑ ነው። ይፍጠንም ይዘግይ አንድ ቀን ወደ ድል ጎዳና የምናደርገውን ጉዞ ይመሩልናል በምንላቸው ፖለቲከኞቻችን በኩል ሲቀለድብን የምሩ ይቅርና የማሽላውም ሳቅ ቅንጦት ይሆንብናል።

የመለስ ዜናዊን የጭቆና ቀንበር እንደግለሰብ ከራሳቸን፣ እንደሕዝብ ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ አውርደን ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓት እንዘረጋለን ብለው በአገር ውስጥ ከኛው ጋር የአገዛዙን የግፍ በትር ችለው እየታገሉ ላሉ የፖለቲካ ሃይሎች እውነተኛ አክብሮት አለኝ። ወቀሳዬም ሆነ ትዝብቴ የሚመነጨው ከዚሁ አክብሮቴ እንጅ ከጥላቻ ወይም ከንቀት የሚመነጭ እንዳልሆነ ቢገነዘቡልኝ ደስ ይለኛል። ይልቁንም ከእኔና ከመሰሎቼ ፍርሃት እና ዝምታ አንፃር ስመለከተው ከእንዲህ አይነት ጨካኝ እና አምባገነን ሥርዓት ጋር ለመላተም ያሳዩት ወኔ እና የደረሰባቸው ስቃይ ታሪካዊ ሥፍራ የሚያገኝ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም።

ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ምርጫው የሚገቡ እውነተኛ ተቃዋሚዎች(በርግጥ እውነተኛ ከሆኑ) አውቀውም ሆነ በቸልታ ሁለት አሁናዊም ታሪካዊም ሊባሉ የሚችሉ ስህተቶችን እየፈጸሙ ነው ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው ምርጫው ላይ በመሳተፍ ሊያገኙ ከሚችሉት ትርፍ ወይም ሊደርስባቸው ከሚችል ኪሳራ ጋር የተገናኘ ነው። በምርጫ 97 የተገኘው ሕዝባዊ ድል በህወሓት ማንአለብኝነት ከተቀለበሰ በሁዋላ የምርጫ ሂደት የሚፈልጋቸው መደላድሎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንደፈረሱ ለተቃዋሚዎች መንገር ለቀባሪው አረዱት ቢሆንም እናገራለሁ። ለአፈና ሥርዓቱ ፅኑ መሰረት የሚሆኑ ህጎች በወጡበት፣ ሚዲያው ክፉ አስም እንዳለበት አረጋዊ በታፈነበት፣ የፍትህ ሥርዓቱ (ድንቄም ሥርዓት) በገዢው መንግስት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ለይሉኝታ ያህል እንኳ ለአፍታ ነጻ በማይመስልበት (በማይሆንበት አላልኩም- ኢሕአዲጋዊ ባህሪው ስለማይፈቅድለት)፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ረገጣው ጫፍ መድረሱን እኛ እየኖርነው የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ደግሞ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማቶቹ በኩል ባረጋገጠበት ወቅት ተቃዋሚዎች ወደምርጫ እየገቡ መሆኑን ቢያውቁትም እገልጸዋለሁ። ዛሬ ተበዳዮች እንደምርጫ 97ቱ ቅሬታዎችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ የፍትህ ሥርዓቱን እንፈትናለን፤ የምርጫ ቦርድን ገመና እናጋልጣለን፤ መንግስትን ፋታ እናሳጣለን ወዘተ እየተባለ አገዛዙን እሚገዳደሩበት ጊዜ ላይ እንዳልሆኑ ሊያውቁ ይገባል። በዚህ ረገድ ከድል ወዲህ ያሉ መለስተኛ የፖለቲካ ትርፎች የሚገኙበት ሁኔታ አይታየኝም። ምክንያቱም ከመነሻው እነዚህ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚፈልጋቸው ተቋማት የመንግስት የቁጥጥር ማነቆ አላላውስ ያላቸው መሆኑንና ለተቋቋሙበት ዓላማ ያላቸው ውክልና ከቀድሞውም በባሰ ደብዛው የጠፋባቸው መሆኑን እኛም ሌላውም ዓለም አውቆታል። ለዚህ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ዝርዝር ሪፖርቶች፣ የነ ዘኢኮኖሚስትንና መሰል ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎችን የሁኔታ ትንታኔ (Situational Analysis)፣ የአሜሪካ መንግስትን ተደጋጋሚ መግለጫዎች ወዘተ ዋቢ መጥቀሱ አይገድም። እነዚህ ተቋማት የመለስ ዜናዊ መንግስት የቆመበትን አምባገነናዊ መሰረት በሚገባ የተረዱት ይመስለኛል። ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀን ምርጫ ትንሽም ቢሆን ተጠቃሚ ሳይሆኑ እውነተኛ ተቃዋሚዎች በምን ስሌት ሊገቡበት እንደፈለጉ ቢያንስ ለእኔ ዓይነት ደጋፊዎቻቸው ግልጽ ሊሆንልን ይገባል።

ሁለተኛው የቧልቱ ገጽታ የተቀዋሚዎች የርስ በርስ ትርምስና ጥል ነው። አንዳንድ የተቃውሞ ሃይሎችና የትግል መሪዎች የምርጫ ድራማው ሳያንስ ትግላቸውን አተካራ የበዛበት ራስ- ወግ የክፍፍል ገቢር ጨምረውለታል። ለነዚህ ወገኖች ብዙዎቻችን የምናስተላልፈው መልዕክት አጭርና ግልጽ ይመስለኛል- አዝነንባችኋልና በዳግም ሕብረት ካሱን የሚል። “ዝም አንልም” እያሉ የኢሕአዲግን ድግስ እያደመቁለተ ላሉትም ሆነ በጨዋ ደንብ በመመካከር ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኝነቱ ለጎደላቸው አመራሮች “አዝነንባችኋል” ነው የትዝብታችን መነሻ። ለህወሃት/ኢሕአዲግ ቧልት እያበረከታችሁለት ያለው ትዕይንታዊ አስተዋጽኦ ራሱም ከጠበቀው በላይ ሆኖለት ሲዝናናብን እኛ ተስፋ የሰነቅንባችሁ ዜጎች ግን ቧልት አለሰገባው ገብቶብን አልተመቸንም። ተቃዋሚዎች ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሳሎናቸው ባቢሎን ሆኖ እያየንና የጣልንባቸው እምነት በእጅጉ ተፈትኖ እያለ ቤታቸውን ሳያስተካክሉ ምርጫ ውጡ ሊሉን አይችሉም ባይ ነኝ - Keep your house in order እንዲል ፈረንጅ። ጊዜው ሕብረታቸውን ከምር ለማጠንከር የሚሰሩበት እንጂ የመለስ የምርጫ ተውኔት አሳላጭ ሆነው መሳቂያ መሳለቂያ የሚሆኑበት እነዳልሆነ እንዲሁም ለአምባገነናዊ ስርዓት ህጋዊ መሰረት ላለመስጠት ጥንቃቄ ሊያደርጉ የሚገባበት እንደሆነ ነጋሪ ሊያስፈልጋቸወ አይገባም።

ለዚህ ሥርዓት መጠናከር አውቀውም ሆነ በግዴለሽነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ፖለቲከኞቻችን የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ልባዊ ድጋፍ እንደሚያጡት ሊያውቁት ይገባል። ሥርዓቱ በርሃባችን የሚያላግጥ፣ በነጻነት ጥማታችን ላይ የሚያላግጥ ብቻ አይደለም፤ ተርበንም ሥርዓቱ የፈጠራቸውን ዘመነኛ ጥጋበኞችን ቤት እንዳንሰብር፣ ጓዳ ጎድጓዳቸውን እንዳንበረብር አድርጎ ያሳደገንን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጭምር የሚንቅና የሚያጥላላ ሥርዓት ነው። ሥር በሰደደ የአድልዎ አሰራር ሥራ አጥ ቀፍቅፎ አደገኛ ቦዘኔ እያለ የሚሰድበን፣ በፖሊስና ‘ደህንነት’ መዋቅሩ ህግ አልባ በትሩ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣን መንግስት እንደመሆኑ መጠን ልንታገለው ሥንረባረብ “አባሎችና ደጋፊዎች ቢታሰሩብንም፣ መሪያችን ያለሕግ ወህኒ ብትወርድም፣ የስብሰባ አዳራሽ ባይፈቀድልንም፣ ከህዝብ ጋር ተገናኝተን እንዳንወያይ እየተደረግን ብንሆንም ወዘተ” የሚል የዋህ ስሌት በሚያወጡ ሃይሎች አመራር የትም ልንደርስ እንደማንችል ግልጽ መሆን ይኖርበታል።

ይልቁንስ መከፋፈሉ ቀርቶ ለአዋጭ የትግል ስትራቴጂና ስልት መተባበሩ ያዋጣል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ፈታኝ ዘመናትን የተሻገራቸው በህብረቱና በአንድነቱ ነውና ይህ አንድነት በተለይ በአገር በቀል ጠላት የአመታት ሴራ እንዳይላላ (የልዩነት ጥላው እንዳጠላብን እናውቃለንና) መስራት ያለባቸው ወገኖች ልዩነታቸውን አቻችለው አገራችንንና ህዝቡን የመታደግ ተግባር ለመፈጸም መረባረብ ቀዳሚ ሥራቸው መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። “ኢህአዲግ ከፋፈለን” በሚል ሰበብ ሳይጠፋፉ የትብብር ሥራው የምርጫ ዘመቻውን ሊቀድም ይገባል። ያን ጊዜ የተሰራብንን አዲስ የዘር መራሽ ሥርዓት ማገር ሆነን ባለማጥበቃችን ግፍ እየዋለብን ያለውን ጎጠኛ አገዛዝ መጣል እንችላለን። ይህ ካልሆነ ግን በዘር መዋቅሮቹ አማካይነት የሚዘርፈንን ፣ በጥይት አረር የሚቆላንን፣ በችግጋር አለንጋ የሚገርፈንን አገዛዝ አሁን በተተበተብንበት የክፍፍል መረብ ውስጥ ሆነን መውጫችንን ሳንተልም በቧልታይ የምርጫ ተውኔት ማስወገድ ይቅርና ማሻሻል አይቻለንም። በችጋር ከሚገርፈው ህዝብ ሰቆቃ ሳይቀር በርዳታ እህል መያዣነት ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲሞክር ሀፍረት ለማይሰማው አገዛዝ፣ “የሞተው 193 ሰው ብቻ ነው፤ የተራበው 6 ሚሊዮን ብቻ ነው” ወዘተ በሚል አሳፋሪ መከራከሪያ የኢትዮጵያን ህዝብ ሥቃይ ከስታትስቲካዊ ዋጋው አሳልፎ ለማያይ ሥርዓት ህጋዊ መሰረትን ሊያሰፋ ለሚችል ምርጫ መሽቀዳደሙ ከእውነተኛ የዲሞክራሲ ሃይሎች የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። በተለይም ከመራጭ ህዝብ ጋር ተገናኝቶ የምር ለመወያየት ባልተቻለበት፣ የምርጫ ሂደት የሚፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለምልክት ያህል እንኳ በማይታዩበት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎች በጨዋታው ሜዳ አይነትና ምንነት ላይ የመደራደር አቅማቸው በተሟጠጠበት ሁኔታ ወደምርጫ መግባት የዋህነት ከፍ ሲልም ራስ ወዳድነት ይመስለኛል።

እንደ መውጫ
ይህ እንግዲህ የአንድ ተራ ታዛቢ አቋም ነው። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የምር ለሆነ ፀረ-ህውሃት/ኢህአዲግ ትግልና ለትግሉ አራማጆች አድናቆት አለኝ። በመሆኑም ምርጫው የፈታኙ የትግል ሒደት አንድ አካል ስለሆነ የሚገኝበት ጥቅም ይኖራል ብለው የሚያምኑ እውነተኛ የዲሞክራሲ ሃይሎች ካሉ ሃሳባቸውን አከብራለሁ። ይሁንና በዚህ ቀመር ወደ ምርጫው የሚገቡ ወገኖች ከተሳትፎው የሚገኘውን ተጨባጭ ጥቅም በግልጽ ሊያስረዱን ይገባል። አሳማኝ የሆነ ምክንያት ካላቸውና ሂደቱ የሚፈጥራቸውን መልካም አጋጣሚዎች ከአብራሩልን እንዲሁም ድምጻችን እንደማይሰረቅ ያለንን መተማመኛ ከአመላከቱን ምናልባት ወጥተን እንመርጣቸው ይሆናል። ይህ ግን አሁን ባለኝ ግንዛቤ የሚቻላቸው ስለማይመስለኝ ምርጫው እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ቅዠት የለኝም። ስለዚህ በእኔ እይታ ገዢው ፓርቲ ጥቅሙን በሚገባ አስልቶ ለእይታ ሊያበቃው ተፍ ተፍ ከሚልለት የምርጫ ቧልት ተቃዋሚዎች ሊመዙት የሚችሉት የቁም ነገር ሰበዝ የምርጫ መድረኩን ጥሎ በመውጣትና ለፌዝ ድግሱ ዕውቅና በመንሳት ቆራጥ ርምጃ ላይ የተንጠለጠለ ይመስነኛል።

ይኸይስ ሞረዳ - ከአዲስ አበባ

No comments: