Friday, July 24, 2009

ጮክ ብለህ ተናገር (Speak out)

By: ዳግማዊ ዳዊት

ልቤ እስከሚሸብር- መልካው እስኪናጋ
ወፎች ግ…ር እስኪሉ-እስኪበተን መንጋ
ጀግና እስከሚፎክር- ፈሪ እስከሚያመልጠው
ልጆች እስኪሮጡ- መዓት መጣ ብለው
ቄሱ እስከሚያማትብ- እስኪል “በሥላሤ”
ሠባኪው እስከሚል- “በጌታ እየሱሴ”
ሸኩ “ያ--አላህ” ብሎ- አዛን እስኪያሰማ
ሾፌሩ ለመሄድ-ለመቆም ሲያቅማማ
እናት “ውይ” እስክትል- ደረቷን ስትመታ
ሌባ እስኪበረግግ -እስኪሮጥ በአፍታ
እስከሚያስተጋባ- ሸንተረር ሸሎቆው
ተራራና ወንዙ- ዛፉና ቁጥቋጦው
ጮክ ብለህ ተናገር- እኔም ልበል አሜን
እስካዳነ ድረስ- ሃገሬን ወገኔን
ላይጠራ አይደፈርስ- ሣይጨልም አይነጋ
በለው ተናገረው- መልካው እስኪናጋ።

መነኩሴው ሲረሸን- ቤተመቅደስ ገብቶ
ዔሎሄ ሃገሬ- ዎገኔ እሚል ጠፍቶ
ሚስት ስትገደል- ሥለባሏ ጮሃ
ወገኔ በሥደት ሲሞት በበረሃ
አዛውንት ሲታሰር- እህት ስትደፈር
ፍትህ ሥትዛባ- ሃይማኖት ሥትሻር
ዝምታው ምንድን ነው- ተናገር ላዳምጥህ
ወርቅ ነው እሚነጥር- አንጥረው ተናግረህ።

የውንድምህ ግጭት- ያኮረፍክበቱ
አያስደነግጥም- ቢታይም ውጤቱ
ሃገር አያጠፋ- አይገድል ወገን
“ያዝ ..ያዝ” መባባሉ ማውራት ይህንን
ለእኔ ይመስለኛል- ጊዜ ማባከን
እንኳንስ የስው ልጅ- እኩይ ምላስ ያለው
ድንጋይም ይጋጫል- የማይናገረው።

ይልቅ፤
ሰላምን ሥትሻ- ፍትህ እና መብት
ፍቅርን በልብ ይዘህ- ስትል ለእኛ መንግስት
ይህን ስትጠይቅ- በአንተ በፈረደ
አንተ ስትገነባ -እራሱ እየናደ
ያለውን ታገለው -“መለስ” የሚሉትን
ሀገር አፍራሽ ይጥፋ- ቅድሚያ ለእርሱ ይሁን።

ዝምታ ወርቅ ቢሆን- ቢያስከብር በወገን
አክባሪው ሲገደል- ዝምታ ምን ይሆን?
ድሮም ይባል ነበር- ለመሾም በመንበር
ዝምታ አይሆነውም- ከመናገር በቀር
መሾም አይገኝም- ደጃዝማችነቱ
በመናገር ጥረት- የምትገኝቱ።

ግና፡
መቋመጥ ለመውጣት- ከስልጣን ኮርቻ
ላገር ሳይሞቱላት- ልክ እንደነ ባልቻ
እንደነ አባ ታጠቅ- እንደነ አባ ዳኘው
እንደነ አባ በዝብዝ- እንደነ አባ ዳጨው
እንደነ አባ መላ- እንደነ አባ ውቃው
እንደነ አባ ኮስትር- እንደነ አባ ነጋ
እንደ ዘረዓይ ደረስ- እንደነ አብዲሳ አጋ
ካላወጡ ወገን- ከጠላት መንጋጋ
መናገር ቧልት ነው- የመለፍለፍ ዓመል
ሐኪም የሚያሰኘው- ቃልቻ ወይ ፀበል

እና፤
ጮክ ብለህ ተናገር- እኔም ልበል አሜን
እስካዳነ ድረስ- ሃገሬን ወገኔን
አሳርግ ለፍትህ- ለሰላም ለመብት
ለአገር ብልፅግና-ለወገን ለአንድነት
ላይጠራ አይደፈርስ- ሣይጨልም አይነጋ
ጮክ ብለህ ተናገር- ዙፋኑ እንዲናጋ።


ዳግማዊ ዳዊት
ሐምሌ 2001
ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: