ገና ያላየነው-ገና ያልበቀለ
በዚህ አለም ሰዎች- ያልተመረመረ
ማሳው ያልታረሰ- ገና ያልተዘራ
ተሰልፎ ያለ- ከማናውቀው ጎራ
አንገትም ያልለየ- ገና የማይታይ
“ላም አለኝ በሰማይ- ወተቱንም አላይ”
አይደለምወይ ነገ- ያላየነው ሲሳይ?
ጨለማው ብርሀን- ካልሆነልን ዛሬ
ሆነን እያለፍን- ለግፈኛ ሎሌ
ሞተን ሳለን እኛ-እንዴትስ ተኖረ
የመቃብር ኑሮ-ኑሮ እየተባለ
እስከመቸ ድረስ-አንዲህ ይኖራለ?
በግፈኛ አገዛዝ- ወገን እየሞተ
ይህን ኑሮ ብሎ- ማንስ ተደሰተ
አምሳያ መሪያችን- አንገት እየቀላ
ደም እየፈሰስ-በአዲስ በጋምቤላ
ሰው እየታረደ-በአይደር በባህርዳር
በጅማ በደሴ -ደብረ ታቦር ጎንደር
አሰቦት በደኖ-አሶሳና ህረር
መቐለና ማርቆስ-አዋሳ ኦጋዴን
ማለፉ ምንድን ነው- ሳንኖረው ዛሬን?
“ነገ-ነገ” አትበሉኝ-ዛሬን ነው እምንኖረው
ነገ የኛ አይደለም- የሌላው ተራ ነው
ዛሬን ነው እምንኖረው- ዛሬም ነው እምናልፈው።
አውቃለሁ ወገኔ- አትደከም አትልፋ
ትናንት ትዝታ ነው- ነገም ደግሞ ተስፋ
ምን ዋጋ አለው ነገ- ወገኔ ከጠፋ-ሃገሬ ከጠፋ
እንዴትስ ሊደረስ- እንዴትስ ልንኖረው
የኛ ተራ ዛሬ- ነገም የሌላ ነው።
ዛሬ ምን አግብቶት- በነገ ጉዳይ
ነገ-ነገ አይደልዎይ-የሚያድር ሲሳይ
በምን አቆጣጠር- በማንስ ቀመር
ምን አገባው ነገ-በዛሬ ነገር
ቢቆጠር አበሳው-ቢቆጠር ክፋቱ
የማናውቀው መልአክ- ነገ የሚሉቱ
ያስፈራ የለምዎይ- ከዛሬ አጋንንቱ?
ፈጣሪ የሰራው-እንደኔው ፍጡር
አላስኖረኝ ካለ- በአምላኬ ምድር
ምን አለኝ ብየ- ነው ለነገ ማሰቤ
ዛሬን መኖሬ ነው-የመኖር ማተቤ።
አይደለም አትበሉኝ- ፈቃደ ሥላሴ
ተጠባ ተጭንቃ- ተወጥራ ነፍሴ
አምላኬ አይዎቅሰኝም- ስለዚህ ተግባሬ
ሃጥያት አይሆን ፍጹም- ለዛሬ መጣሬ
“ኢንሻ አላህ” ብትሉኝ “በጌታ እየሱስ”
የዛሬ ምኞቴ-ዛሬው እንዲደርስ
ሃገር ነጻ ብትሆን- ከአገዛዝ መለስ
ጽድቅ ይሏል እርሱ ነው-መኖር መቻል ዛሬ
በነጻነት መኖር- በኢትዮጵያ ሀገሬ።
ሐምሌ 2001
ዳግማዊ ዳዊት
Ethio_dagmawi@yahoo.com
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment