Wednesday, July 22, 2009

ከወያኔ ዘረኛ እምነቶችና ድርጊቶች ምን እየተማርን ነው። የዘረኛነትን አደጋ ለመታገል ምን ማድረግ እንችላለን?

አንዳርጋቸው ጽጌ
(ሐምሌ 5 ቀን 2001 ዓም፣ ሚነሶታ አሜሪካ በግንቦት 7 ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የቀረበ ንግግር)

እያቆሰለንና እያደማን ስለመጣው የወያኔ ዘረኛነት ሁላችንም እናውቃለን። ዝርዝሩን ማቅረብ አያስፈልግም። ይህ ዘረኛነት እያስከተለ ስላለው መዘዝና ሁላችንም ይህንን መርዘኛ መዘዝ ለመታገል ምን ማድረግ እንደሚገባን ጥቂት ከማለቴ በፊት ለመግቢያ ወይም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ለመዋዣ እንዲሆነን በሚቀጥለው ነጥብ ልጀምር።

ወደ አሜሪካ ጉዞዬን ስጀምር የጉዞ ባልደረባዬ እንዲሆን የመረጥኩት መጽሃፍ የታዋቂውን ሩሲያዊ የፈዮዶር ዶስቶቭሰኬ ዘ ብራዘርስ ካራማዞቭ የተሰኘውን መጽሃፍ ነበር።

የኔ ትውልድ እንዲህ አይነቶቹን መጽሃፍት የማንበብ ልምድ የነበረው ቢሆንም እያደር እንደተረዳሁት እነዚህን መጽሃፍት ያነበብንበት እድሜያችን፤ የህይወት ተመክሮአችን፣ ያነበብነበት የአእምሮ ቅላጼ/mind set፣ የቋንቋ ችሎታችን ደካማነትና ሌሎችም ነገሮች በአንድ ላይ ተደምረው፤ የእነዚህን ድንቅ ስነጽሁፎች ለዛና ውበት አጣጥመንና መልክቶቻቸውንም ተረድተነው ነበር የሚል እምነት እንዳይኖረኝ አድርገውኛል። በእዚህ የተነሳ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እነዚህን መጽሃፍት እንደገና ማንበብ ጀምሪያለሁ። እየገረመኝ ያለው ነገር በወጣትነት እድሜ ያላየሁዋቸው በርካታ ቁም ነገሮች በእነዚህ መጽሃፍት ውስጥ ማየት መጀመሬ ነው። ታላላቆቼ ‹‹ህይወት ትምህርቱ የማያልቅበት ዩኒቨርስቲ ነው›› ሲሉ እየሰማሁ በማደጌ በልጅነት ድንቁርናዬ መገረም የለብኝም።

ዶስቶቭስሲ ዘ ብራዘርስ ካራማዞቭ በተሰኘው መጽሃፉ ውስጥ አባ ዞሲማ የተባሉትን አረጋዊ ገጸ ባህርይ፤ አንደበቱ አድርጎ ‹‹ገሀነብ ምንድነው››? የሚል ጥያቄ አንስቶ ምላሹን በእኝሁመንፈሳዊ ሰው አንደበት ሲመልስ እንዲህ ብሎናል።

‹‹ገሃነብ ማለት የሰው ልጅ ለማፍቀር/ለመውደድ ያለው ተፈጥሮው በመስረቁ/በመሟጠጡ የሚገጥመው መከራ/ስቃይ ማለት ነው።›› ይለናል።

እውነቱን ልንገራችሁ፤ ወገኖቼ!!
ስለገሃነብ ብዙ ትርጉሞች ሰምቻለሁ እንደእዚህ የገሃነብ ትርጉም ግን አእምሮዬ ውስጥ ተቀርቅሮ የቀረ የለም። አእምሮዬ ውስጥ ተቀርቅሮ የቀረው ግን ያለምክንያት አይደለም። በግሌ ለአባባሉ ትልቅ ክብደት እንድሰጥ ያደረገኝ ወያኔ ስልጣን በሃገራችን ከያዘ ጀምሮ በሃገራችን የከፈተው ፈታኝ ዘመን ነው። የወያኔ የዘር ፖለቲካ ስብእናችን እየሰረሰ በአንድ ሃገር ውስጥ የምንኖር ዜጎች አንዳችን በሌላው ጥርጣሬ እንዲኖረን፣ አንዳችን የሌላውን ውበት ማድነቅ፣ የሌላውን ሳቅ መሳቅ የሌላውን ስቃይ መቁሰል በማንችልበት የጥላቻ እስርቤት ውስጥ እየጨመረን ነው የሚል ስጋት ስለሚሰማኝ ነው።

ምንም ነገር እንደራስ ልምድና ተመክሮ አስተማሪነት ያለው ስለማይሆን ይህንን ሰጋቴን ለመግለጽ ከራሴ ታሪክ ልነሳ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2005 ሰኔ ወር ከምርጫው በኋላ፣ ትግርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ያሉበት የወያኔ ሴኩሪቲ አፋኝ ቡድን ዛሬ በ80 አመቱ ቃሊቲ ወህኒ ቤት የተጣለውን የአባቴን ቤት አጥር ዘሎ ገባ። በግቢ ውስጥ በሚኖረው በርካታ ህዝብ ላይ ሽብር ፈጠረ። እኔን ወደ እስርቤት ሲወስድ፤ እዛው ግቢ ውስጥ ቆሞ ሁኔታውን በሚመለከተው አባቴና ሌሎች በግቢው ንዋሪዎች በሆኑ በርካታ ግለሰቦች ፊት አንዱ በያዘው ዱላ ጀርባየና ማጅራቴ ላይ መታኝ። የገረመኝ ዱላው አልነበረም።


ለምን ትማታለህ? የጠየቃችሁኝ አላደርግም አላልኩ? በማለት በዱላ ለመታኝ፤ በእድሜው ወጣት ለነበረው የወያኔ ሰላይ ጥያቄ እቀረብኩ። ሰውየው የሰጠኝ ምላሽ አስገራሚ ነበር። ከ15 የሚበልጡ ሰዎች እየሰሙት ‹ደብድቡት›› የሚል ትእዛዝ ተሰጥቶናል ነበር ያለው። ዱላው በእዚህ አላበቃም። አራተኛ ፖሊስ ጣብያ ከተወሰድኩ በኋዋላ ስድስት የደህንነትና የፌደራል ፖሊስ አባላት በዱላ በጠመንጃና በሽጉጥ ሰደፍ ሲቀጠቅጡኝ እርስ በርሳቸው በትግርኛ ቋንቋ
እየተናገሩ ነበር። የራሳቸውን ዘር እየቀጠቀጠ የመግዛት መብት እንዳለው፤ ለእዛም መብት ያበቃቸውን የተለየ ጀግንነት የተላበሱ መሆናቸውን በድንፋታ እየተናገሩ ነበር ዱላውን የሚያዘንቡብኝ። በደህና ቀን የተማርኳት ትግርኛ ባለጌ ስድባቸውን ለመስማት አስቻለችኝ። እንደእውነቱ ከሆነ የሰማሁትን ከሰማሁ በኋላ ጆሮየን ቢቆርጡኝ ትግርኛ የማልሰማ ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር።

በእዛ እለት በአዲስ አበባ ንጹሃን የህዝብ ደም የሰከሩት የወያኔ ነፍሰ ገዳዮች ሁሉንም ዘር ነበር የሚሳደቡት። ለብሄር እኩልነት ቆሚያለሁ እያለ ከሚነግድ የድርጅት አባላት፤ በአደባባይ እንዲህ አይነቱ ዘረኛ ንቀት ለሁሉም የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ይገለጻል ብዩ አስቤ አላውቅም ነበር። በተለይ አማራ ብለው የሚጠሩትን ዘር እጅግ አጸያፊ ከዘር ጋር የተያያዘ፣ እዚህ ለመድገም የሚቀፍ ስድብ እየተሳደቡ ነበር የዱላ የርግጫ የካራቴ ናዳ ያወርዱብኝ የነበረው። ልብ በሉ ዘር የምለው ቃላት ያለምክንያት አይደለም። እነዚህ የወያኔ ሰዎች፣ ሰዎችን በደምና በአጥንታቸው እየቆጠሩ ወገናቸው አድርገው እንደሚያዩ ሁሉ ሌላውንም አጥንቱንና ደሙን መርምረው በዘሩ ጠላት አድርገው የሚፈርጁ ናቸው። ይህ ደግሞ ባለፉት አመታት ድርጊቶቻቸው የበለጠ ገሃድ የወጣ ተፈጥሮአቸው ሆኗልና የሚያከራክር አይደለም።

ወደ ደብዳቢዎቼ ስመለስ ግማሽ ፊቴን በሰደፍ አፍርሰው ኮማ ውስጥ ጨምረውኝ በጭቃ እጨቀየው የፖሊስ ጣቢያው መሬት ላይ ጥለውኝ ሄዱ። በዘር ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ብልግና የሞላውን ድርጊታቸውን የፈጸሙት ከ700 እስከ 800 መቶ የሚሆን እስረኛ ፊት ነው። ዱላው ምንም አላማ አልነበረውም። ጥየቄ የለም። ምንም ነገር የለም። ደብድቡት የሚል ትእዛዝ የተላለፈው በወቅቱ ቅንጅትን በመደገፌ ብቻ ነበር። የኔን መንፈስና ቅስም ለመስበር ነበር።
ሌላውንም በአብዛኛው ወጣት የነበረውን እስረኛ ለማሸበር የተደረገ በጭካኔና በእብሪት የተሞላ ድርጊት ነበር።

በድብደባው የተነሳ ስንት ሰአት ወይም ደቂቃ ኮማ ውስጥ እንደቆየሁ አላውቅም። ከኮማ ስወጣ ግን ያገኘሁት ማንነቴ፤ ኮማ ውስጥ ከመግባቴ በፊት ከነበረኝ ማንነቴ የተለየ ነበር። ለደብዳቢዎቼ ብቻ ሳይሆን ከደብዳቢዎቼ ዘር ጋር ለተገናኘ ማንኛያውም ሰውና ነገር ከፍተኛ ጥላቻና ምሬት ልቤን ሞልቶት አገኘሁት። ከሚደበድቡኝ 6 የመለስ ዜናዊ አሽከሮች በላይ የሚሻገር ከሰዎቹ ትግሬነት ጋር የተሳሰረ ለዘራቸው በሙሉ መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገ ጥላቻ ስብእናየን እንደአሲድ ሲበላው አገኘሁት። በጣም የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ የሚያሳዝንና የሚያበሳጭ ስሜት ነበር።

በግሌ የማውቀውን የትግራይ እናቶች ደግነትና ሩህሩህነት፣ የትግራይ አርሶ አደር ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ከህሊናዬና ከልቤ ፍቆ ማንኛውን ከትግሬነትን ጋር የተያያዘ ነገር በጠላሁበት ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ራሴን ከሳትሁበት ሁኔታ የነቃሁት። ይህ ነበር ያሳዘነኝና ያበሳጨኝ። እነዚህ ዘረኞች እኔንም እንደእነሱ ስብእና የሌለው አውሬ ሊደርጉኝ ነው በማለት ነበር የተናደድክት። እንግዲህ አስቡት እኔ በቅርቡ ብዙ ነገር ስለትግራይ ህዝብ ምንነት የማውቅ ሰው፣ እንዳውም ከደርግ ጥይት ሸሽቴ መጠለያዬ የሆነኝን፣ በኋላም ከረሃብ ከወባ ከተስቦ ተርፌ በህይወት
እንድሰነበት በመሃከሉ አኑሮ፣ ከእዛ በችግር ከተሞላ ህይወቱ ያለውን አካፍሎ መልሶ ሰው ያደረገኝን የትግራይ ማህበረሰብ በአንድ ጨፍልቄ ለዘር ማንዘሩ ጥፋት ከተመኘሁ ሌላው የእኔ አይነት የህሊና ወቃሽና አስተዋሽ የሌለው ተመሳሳይ በደል የሚደርስበት ዜጋ ምን ሊያስብ እንደሚችል ገምቱት። በለመስ ዜናዊ የወያኔ ወታደሮች ቤቱ የተቃጠለው፤ የታረደው፣ ሚስቱን ወጣት ሴት ልጁን የተደፈረው፣ መንድሩ የጋየው፣ በገፍ የተጋዘው፣ የተዋረደው፣ የተዘረፈው፣ የዘር ማጥፋት እርምጃ የተወሰደበት መላው የሃገሪቱ ህዝብ ምን ይሰማዋል?

በእዚህ ስራ በዋንኛነት መለስ ዜናዊ የሚያሰማራቸውም የሚያምናቸውም የወያኔ ሰዎች በሙሉ የትግራይ ሰዎች ናቸው። ያው ሁላችሁም በቅርቡ ዝርዝሩን እንዳያችሁት ወታደራዊና የሴኩሪቲ ተቋማቱን በሙሉ የተቆጣጠሩት ወያኔዎች ናቸው። ከእነዚህም መሃል ከሌሎች ብሄሮች የተቀላቀሉ ጥቂት ወታደሮችና ደህንነቶች ቢኖሩም ዋናውን ስልጣን ይዘው ፍለጠው ቁረጠው ግደለው እሰረው ዝርፈው የሚለውን ትእዛዝ የሚያስተላልፉት የትግራይ ተወላጆች የወያኔ አባላት ናቸው።

እነዚህ ሰዎች የሚፈጸሙትን ግፍና አበሳ ሆን ብለው ዘረኛ የሆነ ልባስ ይሰጡታል። ሆን ብለው ስልጣኑ ያለው በእኛ በትግሬዎች እጅ ነው ምን አባክ ትሆናለህ የሚል መልአክት ነው በሁሉም ድርጊቶቻቸው ለማስተላለፍ የሚፈልጉት። ልብ በሉ ስልጣን በእኛ ወያኔዎች እጅ ነው አይሉም። በእኛ በትግሬዎች እጅ ነው የሚሉት። ግፍና በደሉ የሚደርስበት የሃገሪቱ ህዝብ የሚደርስበትን ስቃይ በዘር የተደራጁ ሃይሎች ዘር ለይተው የሚያደርሱበት የዘር ጥቃት አድርጎ እንዲያየው ሆን ብለው ተግተው እየሰሩ ነው። ይህ ጉዳይ ከወታደራዊና ከአፈና ፈርጆች አልፎ በሰልጣንና ሃብት ድልድልም አግጦ የሚታይ ሲሆን ደግሞ ሁኔታው ምን ያህል የከፋና የተወሳሰበ ሊሆን አንደሚችል ገምቱት።

አንዳንድ ሰዎች ይህ ጉዳይ ተደባብሶ አሁን የምሰጠውን ትኩረት አግኘቶ ወይይት እንዲደረግበት አይፈልጉም። በእዚህ እኔ አልስማማም። በበኩሌ ይህ ሸፋፍኖ የመሄድ ጉዳይ የትም አያደርሰንም። እንዳውም በድፍረት በአደባባይ በመነጋገር የወያኔ የዘር ፖለቲካ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ፊታች ላይ ሳይፈነዳ መፍትሄ እንድንፈልግለት ያሽችለናል ባይ ነኝ። እውነቱን ለመናገር ይህ አይነቱ ዘረኛ አመለካከት፤ የመለስ ዜናዊና የወያኔ አባላት ብቻ ችግር ነው የሚል
እምነት የለኝም።

ኋላቀርነትና ድህነት ጠፍረው በያዙት፣ ነጻነትና መብት ባልተከበረበት፣ ህዝብ ከማንኛውም አይነት ጭቆና እራሱን መከላከል የሚችልባቸው የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት በሌሉበት ሃገር ውስጥ የሚገኝ ኋላቀር ልሂቅና ምሁር ወያኔ ስራ ላይ ባዋለው ተመሳሳይ የዘር ፖለቲካ በቀላሉ ለስልጣንና ለጥቅም እበቃለሁ ብሎ የሚያስብ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል።

በእኔ አመለካከት የወያኔ ዘረኛ አመለካከትና ደርጊት፤ ሌላው ህዝብ ወገኑ የሆነውን የትግራይን ህዝብ የሚያይበትን አይን ብቻ አይደልም እያቀላ ያለው። ሌሎችም በሃገርቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዘውጌ ማህበረሰባት ወይም ብሄረሰቦች የየራሳቸውን አክራሪ ዘረኛነት እንዲኖራቸው እያደረገም ነው። ሰዎች ከራሳቸው ዘር ውጭ ሌላውን ማመን የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እየገቡ ለመሆናቸው በርካታ ማስረጃዎች አሉ። በጋራ ሁላችንም በሰውነታችን ብቻ ልንቀበላቸው የሚገቡ፣ ዘርን፤ ቋንቋንና ባህልን ተሻግረው ሊያስተሳስሩን የሚገቡ ጉዳዮችን፤ ለምሳሌ ውበትን፣
ፍትህንና እውነትን የመሳሰሉ ቁም ነገሮች፣ ትርጉም የሚኖራቸው በዘር መነጽር እስካየናቸው ብቻ የሆነበት ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው። ይህ ደግሞ ቀደም ብዩ የጠቀስኩትን ዶስቶቭስኪ የገለጸውን ገሃነብ በሃገራችን መገንባት ጀምረናል ማለት ነው።

እስቲ አስቡት ከፊት ለፊታችን የምናያት፣ የውበት ጸዳልዋ መንገዱን ሞልቶ በሩቁ ያደነቅናት ወጣት አጠገባችን ደርሳ በደንብ ስናውቃት ኦሮሞ/አማራ/ትግሬ ወይም ከእኛ ዘር ውጭ በመሆንዋ ብቻ ውበቷ ትርጉም የሚያጣ ከሆነ፤ በንጽህና ሳቃቸው ልባችንን የሚሰርቁት የህጻናት ድምጽ የሚነካን ህጻናቱ ከራሳችን ዘር መምጣቸውን ስናውቅ ብቻ ከሆነ፤ ለልጇ ሞት አምራ የምታለቅስ እናት ሃዘኗ የሚሰማን የእኛ ከምንለው ዘር ብቻ ከመጣች ከሆነ፤ እስቲ አስቡት ምን
አይነት ሃገርና ማህበረሰብ እየፈጠርን ነው? እውነትም በጥላቻ የተሞላ የመውደድና የማፍቀር አቅማቻን የተሰለበበትን በስቃይ የተሞላውን ምድራዊ ገሃነብ እየገነባን ነው ማለት ነው።

ከልቤ ነው፣ ከወያኔ ዘረኛ እምነትና ተግባር ተምረን በግዜ ሁላችንም ብሄረሰብን/ዘውግን ወይም ዘርን በሚመለከት የያዝነውን የፖለቲካ ቅኝት ለመፈተሽና በእዚህ ከዘር ጋር በተያያዘ ፖለቲካ ውስጥ ያሰፈሰፈውን ለአንዳችንም የማይበጅ የጥፋት መርዝ በግዜ ካልነቀልነው የኢትዮጵያና የዜጎቿ መከራና ጣር ማለቂያ አይኖረውም። አሁን ከምናየው ደረጃ በሽዎች እጥፍ የሚያድግበትን ሁኔታ ልንፈጥር እንችላላን የሚል ስጋት አለኝ።

ወያኔ ዛሬ እራሱ በተግባር እያዋለው ያለው ዘረኛነት እየቀሰቀስ ያለው ቁጣ የተለያዩ መገለጫዎች አሉት። አንዱና አስፈሪ የሆነው መገለጫ የዘር ስሜትን ማጠናከር ነው። በዘር ላይ የተመሰረተን ጥላቻ ማስፋፈትን ነው። ወያኔ የራሱን የዘረኛት እምነት ለማስፋፋትና ዘረኛ የሆነውን አገዛዙን ለማጠናከር የቻለው በሃገራችን ውስጥ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ወይም ዘውጌ ማህበረሰባት የመኖራቸውን ሃቅ ለእኩይ አለማው መጠቀሚያ በማድረግ ነው። ሃገራችንም እነዚህን ዘውጌ ማህበረሰባት ለማሰባሰብ ይሁን የተሰባሰቡትን ይዞ ለመቀጠል የቻለችበት ታሪኳ፤ በስቃይ፣ በመከራ፤ በእንባና በደም የተለወሰ አንድ አሳዛኘ ገጽታ ያለው መሆኑን ሃቅ ለመሰሪ አላማው መገልገያ በማድረግ ነው። ይህንንም የታሪክ ገጽታ ወያኔ መዘርጋት ለፈለገው ዘረኛ ስርአት መጠቀሚያ ለማድረግ ቆርጦ በመነሳቱ ነው።

ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰውንና ለረጅም ዘመናት የቆየውን ፍትሃዊ የሆነ የዘውጎች/የብሄር ብሄረሰቦች የእኩልነት ጥያቄ ወደ ዘር ጥላቻ እንዲቀየር በማደረግ የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ ለመግዛት ተጠቀመበት። ወያኔ ብሄር/ ብሄረሰቦች ወይም የዘውግ ማህበረሰቦች ያነሷቸውን፣ በማእከላዊ መንግስት ጉዳዮች ጭምር የመወሰን መብት ጥያቄ፤ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ፣ ቋንቋን የመጠቀም ባህልን የማበልጽግ ጥያቄ፣ በዋንኛነት ይህ ጥያቄ ከሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቀምቶ፤ ዘመናዊነት ያልቀበረውን የጨለማ ዘመን የትግራይ መሳፍንቶች የስልጣንና የጥቅም ሽኩቻ በአዲስ መልኩ ነፍስ ዘርቶበት ከደደቢት በረሃ ተንደርድሮ አዲስ አበባ ከምኒልክ ቤተመንግሰት ከች ያለ ድርጅት ነው።

ዛሬ በሃገራችን ዜጎች ወይም የሰው ልጆች ምርጫ ሳይኖራቸው የተወለዱበትን የዘውግ ቡድን/ዘር/ ብሄረሰብ፣ ማለትም ኦሮሞነትን፣ አማራነትን፣ ጉራጌነትን፣ ሲዳማነትን፣ አኝዋክነትን መለያ ያደረገ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። የመገደል፣ የመታሰር፣ የመዋረድ፣ ምክንያቶች በዘር መለያ የሚታደል ሆኗል። የመደህየት፣ የመሰደድ፣ በበሽታ የማለቅ እድላቸው፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ሆኗል። ለስልጣን፣ ለሃብት፣ ለከፍተኛ ትምህርት የሚታጩበት ወይም
የማይታጩበት እድል በዋንኛነት በዘር ማንነት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ሁኔታ እኛና እነሱ የሚልን መከፋፈል መፍጠሩ የማይቀር ነው። እራሱን ተጠቃሚ አድርጎ የሚያየው የአንድ ዘውግ ቡድን አገኘሁት የሚለውን ጥቅም በማናቸውም ኪሳራ ለመከላከል ሲሞክር፣ ከጥቅም የተገለለውም ደግሞ በማናቸውም ኪሳራ የተቀማውን ጥቅምና መብት ለማስመለስ ሲታገል መጨረሻው ፍጥጫ ግጭትና እልቂት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ወያኔ በሃገራችን የዘረጋው ዘረኛ ስርአት እንዲህ አይነቱን ሁኔታ በIትዮጵያ ውስጥ በማንገስ ላይ የተመሰረተ ነው።

ወያኔ በጉልበት የያዘውን ስልጣንና ከእዚህም ስልጣን ጋር ተያይዞ የሚያኪያሂደውን አጅግ ዘግናኝ የሆነ ዘረፋ፣ ዘረኛ በሆነ መንገድ ከመግፋት ሌላ አማራጭ የለውም። ይህ ዘረኛነት ሌላውን በዘር ለይቶ መበደል ብቻ ሳይሆን፤ በእዚህ በደል የተነሳ በሌላው ወገን የሚነሳውን ፍትሃዊ ተቃውሞ መቋቋም እችላለሁ ብሎ ወያኔ የሚያምነው ሁሉንም የትግራይ ተወላጅ በወያኔ ስርአት ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ እንዲያምን ሌላውም ህዝብ ይህን እውነት ነው ብሎ
እንዲቀበል በማድርግ ነው። የትግራይ ህዝብ ህልውና፣ ከወያኔ ህልውና ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ያለወያኔ የትግራይ ህዝብ መብቱም ጥቅሙም ህልውናውም እንደማይኖር ለማሳመን በመጣር ነው።

የወያኔ ዘረኛነት በሃገራችን ከእዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ርእዮተ አለማዊ ሽፋን ያለው ዘረኛነት እያስፋፋ ነው። በሃገሪቱ ውስጥ በሚገኙት ህዝቦች የስብእና መዋረድ፣ መራቆትና መደህየት፣ የመብት ገፈፋና ረገጣ ወያኔ የሚያምንበት የትግራይነት ምንነት/ identity መገንቢያ ለማድረግ አቅዶ የሚንቀሳቀስ ነው። ይህንን ለማደረግ የታሪክ ጭብጦችን ማጣመም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚጋራው ታሪክ እንደሌለው መዋሸት ልማዱ ነው። ከእዚህም አልፎ ወያኔ ለአባላቱ የሚያስተላልፈው መልእክት ወርቅና ምርጦች ናችሁና ምርጥ ምርጡ ይገባችኋል የሚል ነው። ወያኔ እየሞከረ ያለው፤ የዘውግ አፓርታይድ/ethnic Apartheid በኢትዮጵያ በመገንባት በዘር አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የተፈረጁ ዜጎች በአንድ ሃገር ላይ ለመፍጠር ነው።

ይህ የወያኔ መርሃ ግብር ምን ያህል ተሳክቷል የሚለው ጥያቄ ሳይንሳዊ መልስ የሚሰጠው ባይሆንም በእዚህ የወያኔ መሪዎች በእብደት የተሞላ እምነት እየተለከፈ ያለውን የሰው ቁጥር ለፖለቲካ ድለላ ብለን ማሳነሱ ተገቢ አይመስለኝም። ይህ መሰሪ የሆነ የወያኔ ድርጊት የማታ ማታ የሚኖረውን አስከፊ መዘዝ በሚገባ ተረድተው በግዜ ወያኔ ዘረኛ በሆነ መንገድ እየበከለ ያለውን የትግራይ ማህበረሰብና ወያኔ ዘረኛ በሆነ መንገድ በሌላው የIትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን አይን ያወጣ በደል፣ ግፍና ዘረፋ መቃወም ያለባቸው በዋነኛነት እራሳቸው የትግራይ ተወላጆች ናቸው። የትግራይ ምሁራንና ዴሞክራት፣ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ከፍተኛ መስዋእትንት እየከፈሉም ቢሆን የወያኔንን ዘረኛ አደገኛ አመለካከትና ድርጊት በተግባር መታገል የሚገባቸው እነሱ ናቸው። ይህን የወያኔ አደገኛ አመለካከትና ድርጊት የሚኮንኑኑን የሌሎች ዘውጌ ማህበረሰብ አባላት በጸረ ትግሬነት መኮነኑን ትተው በቅድሚ ማውገዝ የሚገባቸው የወያኔን ፋሽቶችንና ዘራፊዎችን ሊሆን ይገባል። የጸረ ዘረኛት የቤት ስራችንን ሁላችንም ተባብረን እንድንሰራ ከተፈለገ ይህንን የተቀደሰ የጋራ አላማ በዋንኛነት መምራት የሚገባቸው እነዚሁ አርቆ አሳቢ የትግራይ ምሁራንና ልሂቃን ናቸው የሚል እምነት አለኝ።

ሌሎቻችን ባለንበት ወቅት ማድረግ የሚገባን ጉዳይ ቢኖር ለራሳችን ክብር ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተን ወያኔ በምንም አይንት መንገድ ዘረኛ በሆነ መንገድ አዋርዶ ሊገዛን የማንፈቅድለት መሆኑን በተግባር ማሳየት ነው። የዘረጋውን ዘረኛ ስርአት አወላለቅን በቦታው ሁሉንም ዜጎች፣ ወያኔ ነጻ አወጣዋለሁ የሚለውን የትግራይንም ህዝብ ጨምሮ በእኩልነት የሚያስተናግድ ፍትሃዊ ስርአት ለመመስረት ቆርጠን መነሳት ነው። ይህ አስቸጋሪ ትግል የሚጠይቀውን ማናቸውንም
መስዋአትንት ለመክፈል መዘጋጀት ነው። በቃን የማለት ቁርጠኛነት መያዝ ማለት ነው።

ሌላው ከእዚህ የቁርጠኛነት ውሳኔ ጋር ማድርግ የሚገባን ነገር፤ ከወያኔ ዘረኛነት ምን ተምረናል የሚል ጥያቄ ማንሳት ነው። ይህ ጥያቄ በሃገራችን ልንፈጥረው የምንፈልገው የፖለቲካ ስርአት ወያኔ ከተደፈቀበት የዘረኛነት አደጋ እራሱን አንዴት መከላከል ይችላል? የሚል ሊሆን ይገባዋል።

ከወያኔ ዘረኛ አካሄድ መማር የሚገባን የወያኔ ዘረኛት ባስመረረን ቁጥር እያንዳንዳችን የራሳችንን በዘር ላይ የተመሰረተ አጥር በመስራት ችግሩን ልንፈታወ የማንችል መሆኑን ነው። የዘር አጥር መገንባት የወያኔ ዘረኛነት በጋራ ለመታገል የምንችልበትን ጉልበት በታትነን ከሃገሪቱ ህዝብ 6 በመቶ የማይሞላውን ትግራይን እወክላለሁ ለሚል ኋላ ቀር ቡድን ራሳችንን መቀለጃ በማድርግ ለሚደርስብን ውርደት እራሳችንን ተባባሪዎች አደርገን ማቅረብ ይሆናል። ከወያኔ ጋር የምናደርገውን ትግል እኛም እንደወያኔ በዘር ተከፋፈለን እንግፋው ብንል በዋንኛነት ተጠቃሚው ወያኔ ነው። በሃገራችን ሌላው ቀርቶ ሁለቱ ትልልቅ ዘውጌ ማህበራሰባት ኦሮሞውና አማራው ብቻ በወያኔ መረገጥ በቃን ብለው ቢነሱ፤ የተቀረቱንም ወያኔ የዘር ማጥፋት እርምጃ ሳይቀር የወሰደባቸውን አናሳ ዘውጌ ማህበራት ማስተባበር ቢችሉ፤ ወያኔ አስራ ስምንት አመት ቀርቶ አስራ ስምንት ወር ይህንን አይን ያወጣ ዘረኛ በሆነ መንገድ የተደራጀ ግፍና ዘረፋ እየፈጸመ መሰንበት የማይችል እንደነበር ማወቅ ይኖርብናል።

ሌላው ትልቁ ቁምነገር የወያኔን ዘረኛነት ለመታገል ሁሉም የዘረኛነት ግንብ የሚገነባ ከሆነ፣ ዘረኛ ጦሩን የሚስል ከሆነ፤ በዘረኛ መንገድ ወታደራዊ ጉልበቱንና ሃብቱን አስቀድሞ ያደራጃውን ወያኔን ታግሎ የማስወገድ እድሉ ጠባብ እንደሚሆን ነው። ትግሉ ወያኔ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን በየራሱ ዘር ተደራጅቶ ሊያጠቃኝ ይችላል ከሚል ሌላም ዘር ጋር ጭምር መሆኑ አይቀርምና። ከእዚህም አልፎ በአንድ አጋጣሚም ይህ ወያኔን የመጣል የተለያዩ ድርጅቶች የተናጠል ትግል ቢሳካ መጨረሻው የወያኔን ዘረኛ ስርአት በሌላ ዘረኛ ስርአት መተካት ይሆናል። የእዚህ ውጤት ደግሞ ማለቂያ የሌለው የዘር ፍጥጫ፣ ግጭት ማቀጣጠል ይሆናል። ይህ የሚያስገነዝበን ዘረኛውን ወያኔን ታግለን ለማሸነፍ፤ አሸንፈንም ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች ያለምን መድለዎ በሰላምና በእርጋታ መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር የምንችለው ገና ካሁኑ ዘረኛነትን የዘለለ የፖለቲካ ንድፈሃሳብና አደረጃጀት የሚያስፈልገን መሆኑን
ተገንዝበን ይህንንም እውን ለማድረግ ተግተን ከሰራን ብቻ ነው።

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የወያኔ ዘረኛነት መነሻው ፍትሃዊ የሆነውን የብሄረሰቦች/ የዘውግ ማህበረሰቦች የመብት ጥያቄ በዋንኛነት ከሚመለከታቸው የሃገሪቱ ዜጎች ቀምቶ፤ እነዚህን የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎች ወያኔ ሊገነባው ላሰበው ዘረኛ ስርአት መሳሪያዎች ስላደረጋቸው ነው። ወያኔ ይህን ማድርግ የቻለው የዘውግ ስሜት ሃገራዊ የሆነውን የዜግነት ስሜት በፕሮፓጋንዳም ይሁን በአደረጃጀት ደረጃ እንዲረግጠው ማድረግ በመቻሉ ነው። እኛም ስለፈቀድልነት ነው። በሃገራችን ሁላችንም ፍትሃዊነቱን የምንቀበለው የዘውግ እኩልነት ጥያቄ አንድ አይነት ሃገራዊ መጠብቅ ካልተደረገለት በቀላሉ ራሱን ወደ እኛ እና እነሱ ወደሚሉ ዘረኛ ክፍፍሎች የሚወስድ መሆኑን ካለፉት 18 አመታት ታሪካችን የተማርነው ነው። ደጋግሞ ደጋግሞ እንደታየውም የዘውግ የእኩልነት ጥያቄን ከሃገሪቱ ዜጎች በሙሉ የዜግነት መብት ጥያቄ ጋር ሳያስተሳስሩ ሰዎችን አጥንትና ደማቸውን እየመነዘሩ የሚያሰባስቡ ድርጅቶች ውለው አድረው የሚያጠናክሩት ዘረኛነትን ብቻ ነው።

ይህን አደጋ መጠቆም ፍትሃዊ የሆነው የዘውግ እኩልነት ዴሞከራሲያዊ ጥያቄዎችን እንርሳ፣ እንደሌሉ አድርግን እንቁጠራቸው ማለት አይደለም። የዘውግ/ የብሄር/ብሄረሰብ የእኩልነት ጥያቄዎችን ዘረኛ አመለካከትንና አደረጃጀትን ሳናጠናከር ምላሽ የምንሰጥበትን ሁኔታ እንፍጠር ለማለት ብቻ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው የሁሉንም የሃገሪቱን ዜጎች፤ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ይኑሩ፣ ሁሉም በዜግነታቸው የሚገቧቸውና ሊገሰሱ የማይችሉ መብቶች በማስቀመጥ ብቻ ነው። በእዚህ መብቶች መከበር ዙሪያ ሁሉም ዜጎች በጋራ ታግለው፣ በዜግነታቸው የሚኮሩበት ሃገራዊ የፖለቲካ ስርአት መፍጠር የዘረኛነትን አደጋ መከላከያው ቁልፍ መሳሪያ ነው።

የዘውግ እኩልነት ፍትሃዊ ጥያቄ በሃገር ውሰጥ ዜጎች መብታቸው በመከበሩ የተከበረ መብት መሆኑን ማረጋገጥ ስንችል በዘውግ ማንነታችንና በአንድ ሃገር ዜግነታችን መሃክል ያለው ቅራኔ ይጠፋል። ወያኔ እንደሚለው የአንድ ሃገር ዜግነታችንና የአንድ ዘውጌ ማህበረሰብ አባልነታችን በተፎካካሪነት ወይም በእኩልነት የምናስቀምጥበት ሁኔታ ከተፈጠረ ግን በእነዚህ ሁለት ስሜቶች ማሃከል የሚፈጠረው መሳሳብ ለሁላችንም የጋራ የሆነች ሃገር በመፍጠሩ ስራችን ላይ ትልቅ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። የዘውግ መብቴን የማታከብር ኢትዮጵያ ትበጣጠስ የሚል የዘውግ አባል በተበጣጠሰች ኢትዮጵያ ወስጥ ሰላምና እርጋታ አግኝቶ የራሱን ሃገር ፈጥሮ የዘውግ መብቱን ማስከበር የሚችልበት ሁኔታ እውን ሊመጣ ይችላል ወይ ብሎ ሊጠይቅ ይገባዋል። በበኩሌ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ማየት ስለማልችል የዘውግ መብት እንዲከበር የሚታገሉ ሁሉ ጠንካራና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባትም የእዚሁ ትግላቸው ዋንኛው አካል አድርገው ሊያዩትና ሃላፊነትም ወስደው ሊዋደቁለት የሚገባ ጉዳይ ነው የሚል እምንት አለኝ። ሃገራዊ ፖለቲካ የሚያስተሳስራቸው፣ ለሃገራዊ ዴሞክራሲዊና ፍትሃዊ ተቋማት መኖር በጋራ የሚታገሉ የአንድ ሃገር ዜጎች ከሌሉ፤ ሁሉም የዘውግ ማንነቱን ከዜግነቱ አስቀድሞ የሚቆምበት ሁኔታ ከተፈጠረ የዘረኛነትን ሸርተቴ ማስቆም እንደማንችል ማወቅ ይኖርብናል።

ወያኔ አስካሁን ከነብልግናው በሁላችንም ጫንቃ ላይ መሰንበት የቻለው፣ ሌሎች ዘውጌ ማህበረሰቦችን በተለይ ትልልቆቹን የሃገሪቱን ዘውጌ ማህበረሰባት፤ በዘውግ ፖለቲካ አጥንት ንክሻ ላይ ብቻ እንዲረባረቡ ማድረግ በመቻሉ ነው። ወያኔ ግን የፌደራል አገዛዙን ሃብት፣ ጉልበት ጠቅልሎ የያዘበት፣ የሃገሪቱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለራሱ ዘረኛ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ አድርጎ መቅረጽ በመቻሉ ነው።

ከእዚህ የምንወስደው ትምህርት ግልጽ ነው። ሁላችንም፤ አስከዛሬ ድረስ በራሳቸው የዘውግ ፖለቲካ አጀንዳዎች ዙሪያ ሲሽከረከሩ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን ጨምሮ፣ ሃገራዊ ለሆነው የፖለቲካ ምህዳር ትኩረት መስጠት፤ የወያኔ ኋላቀር አመለካከትና ድርጊት ወደ ነበረበት የታሪክ ቆሻሻ መመለሻው ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ነው።

በተለይ ራሳቸውን በዘውግ የአደራጁ ቡድኖች የዘውጋቸውን አበላት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዜጎች የሚመለከቱ ሃገራዊ አጀንዳዎችን ማንሳት፣ በሃገር ደረጃ የሚፈጠረውን የፖለቲካ ስርአት ቅርጽ መስጠት፣ አልፎ ተርፎም ሃገራዊ ትግሉን የመምራታ ሃላፊነትና ግዴታ አለባቸው። ይህንን ለማድረግ ችሎታው ብቃቱና ሰፊ ህዝባዊ መሰረት እንዳላቸው በፍጥነት ተረድተው ቢንቀሳቀሱ የራሳቸውን የዘውግ አበላት ብቻ ሳይሆን የተቀረውንም ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን የመከራ ቀን በማሳጠር የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና ይኖራል የሚል እምነት አለኝ።

የጸረ ወያኔ ትግላችን እንዲሳካ፤ የሃገራችን በርካታ ትውልዶች የዜግነትና የዘውግ እኩልነት መብቶቻቸው እንዲከበሩ የከፈሉት ማለቂያ የሌለው መስወአትነት ውጤት እንዲፈራ፣ ከድህነት ከስደት መላቀቅ ከፈለግን ወያኔ በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ የፈጠራቸውን በተለይ ከዘር ጋር የተያያዙ አዳዲስ ተግዳረቶች/challenges የሚመጥን የፖለቲካ አመለካከትና የአደረጃጀት ለውጥ ማድርግ ይኖርብናል።

የዘመኑን የፖለቲካ ፈተና ተግዳሮት/ challenge በነባሩ የፖለቲካ አመለካከትና አደረጃጀት እስርቤቶች ውስጥ ሆነን ልናልፈው አንችልም። የኔ ተስፋ ይህ ግንዛቤ በሁላችንም ውስጥ በፍጥነት ተጭሮ በጋራ ትግል የወያኔን ዘረኛ አምባገነናዊ ስርአት በሃጋራችን የመጨረሻው አምባገነናዊ አገዛዝ ለማድረግ የምንችልበት የትግል ምእራፍ በፍጥነት ሲጀምር ማየት ነው። ይህ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የሆነ ድርጊት ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነገሮች
ይታዩኛል።

የግንቦት 7 ንቅናቄ ጥሪ፣ ሁላችንም ይህ ጎደላት በማንላት የIትዮጵያ ውስጥ በዜግነታችን ኮርተን፣ ሁሉም አይነት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ተከብረው ተፋቅረን/ተዋደን የምንኖርባት ሃገር በቅርቡ ለማየት በጋራ ለትግል እንድንነሳ ነው። ይህን በማድረግ ሩስያዊው ዶስቶቭስኪ ካስጠነቀቀን ገሃነብ ራሳችንንና መጪውን ትውልድ ለማዳን በጋራ በወያኔ ላይ እንድንነሳ ነው።

አመሰግናለሁ
አንዳርጋቸው ጽጌ

www.ginbot7.org

No comments: