Sunday, July 26, 2009

ፍችውና ላግባሽ

ዳግማዊ ዳዊት

አንች የልቤ ንግሥት -የእኔ ዴዝዲሞና
የጣና ዳር ሎሚ-የባህር ቄጠማ
ውብ ቆንጆ ውብ ንግስት- የዕኔ ሞናሊዛ
ልቤ ክንፍ አወጣ- ለፍቅርሽ ተገዛ።

ነሽዎይ የወሎ ልጅ- የትግራይ ወለላ
የዳህላክ ደማም- የከረን የአስመራ
የመንዝወርቅ ነሽወይ- የባሌ የአዶላ
የጎንደር ወይንእሸት- የጆቲ የጦና
የጋምቤላዋ አልማዝ-የጅማ የአዋሳ
የአፋር የኦጋዴን-የዱፍቲ የመርሳ
የወልቃይት እንቁ-የሸበል በረንታ
ልቤ ባንች ፍቅር- እጅጉን ተረታ።

ለካስ ያ ባልሽ ነው- ጢቅ ሲል ያየሁት
በስው ፊት የተፋው- ነውርን ነውር ንቆት።
ያ ቁመተ ደሃ- ፀባዬ ዲያብሎስ
አፍንጫ ጐራዳ-ትከሻ አልባ ሞገስ
አይኖቹ ሸውራራ-የማያስተውሉ
ጆሮወቹ ድፍን- ወሬ እማያጣሩ
ጥርሶቹ ዘርዛራ- ሚስጥር አይቋጥሩ
ግብሩ የሳጥናኤል-በአገር የተጠላ
ሽክ የማያቀርበው- ካህን ዎይ ደብተራ
መነኩሴ እሚገድል- አምላኩን ሳይፈራ
ከእናቱ እሚቀማ-ለደሃ የማይራራ
እራሰ መላጣ- ባለጉፋያ ፂም
እኔ አንችን ቢያደርገኝ- አብሬው አላድርም።

አይ ዘመን አይ ጊዜ- ወይ ስምንተኛው ሽ
ሚስቱን ከወንድሙ-ይኸው ተጋራሽ
አንገትን ውሽማ-ባል ዳሌ ተካፍሎ
እንዲህያለ ትዳር- አሳየኝ ዘንድሮ።

አምላክ የመረጠው- የሥላሴ ነብይ
ያሳየውን ነገር- ያኔ ሲተነብይ
“እንዲህ ወደ ራስሽ-ራስ ውጋት ይዞ
ለመዳን ሲያስቸግር-ሲያስጨንቅ ሰቅዞ
ጩኸት ታበዣለሽ- እግዜሩን ልመና
እጅሽን ዘርግተሽ- ለምህረቱ መና ”

የነብዩ ትንቢት- ይፈፀም ነውና
ራስ ምታት ባልሽ-ውጋቱ ውሽማ
አንችኑ ሲጋሩ- በዓለም ላይ ተሰማ።

መቸም ያንች ነገር-ታሪክሽ ቢወራ
እንኳን የዕኔ ቢጤው-የማያውቅ ምርመራ
ተነግሮ የማያልቅ-የሚያስገርም ስራ።
ታቻሃምና ያን ጊዜ- የገናእለት ማታ
ሰው በዓል ሊያከብር- ነጋሪት ሲመታ
ፍሪዳው ሲታረድ- ቅርጫው ሲሰናዳ
ውሽማሽ እንደ ቦምብ- ነገር አፈነዳ
ከከንፈርሽ ወርዶ -ደረትሽን ሻተና
አምባ ጓሮ ፈጥሮ- ጃሎ ሸለለና
ቀውጥ ሆነ ሰፈሩ-ራስሽ ታመመ
ሁልተኛ ጊዜ- ያኔም ተደገመ።

ከንፈርን ውሽማ- ዳሌን ባል ተካፍሎ
አምላክ ጉድ አሳየን- በዓይናችን ዘንድሮ
ከእንዲህ ያለ ነገር-ከእንዲህ ያለ ጉድ
ሚስቱን ከውሽማ-ከሚካፈል ወንድ
ምን ጉዳይ ኖሮሽ ነው- ካባልሽ ያለሽው
ውርደት ከዚህ በላይ- ምን ሲያመጣ አየሽው?

ሰማሁ እንዳስተኛሽ- ከግብጹ ነጋዴ
ከአሜሪካው ቱጃር-ከሱዳን መደዴ
ከቻይና ቃልቻ-ከየመን አዝማሪ
ከዓረብ አንዳውላ- ከአውሮጳ አመንዛሪ
ይህ ባልሽ ይቅርብሽ- ፊትሽን አዙሪ።

እንደኔ እንደኔማ- ልቤ እንደሚወደው
እግዜሩ ፀሎቴን- ወደ ላይ ቢያሰርገው
እኔም ጉልበት ኖሮኝ- መውዜሩን ገዝቸው
ወይ በሽማግሌ- በአገር አስፈርጀ
አንችን ከዚህ ባልሽ-ነጥቄ ወስጀ
ማየት ነው የምሻ- አንች ሆነሽ በጀ።

ወይ ዘማድ አዝማዱ- አንድ ላይ ተነስቶ
ያንን እኩይ ባልሽን -ልኩን አሳይቶ
ውሽማሽ ውንድሙን-በሚገባ ቀጥቶ
ይችል እንደሆነ-ዓይንሽን ሊያሣየኝ
ፍችውና ላግባሽ- ጥለሽው ነይልኝ።

ዳግማዊ ዳዊት
ሐምሌ 2001
ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: