Monday, August 17, 2009

መሪዬን ተኩልኝ (Replace My Guide)

በዳግማዊ ዳዊት

አንድ ምስኪን ደሃ-ማየት የተሳነኝ
ቀኑና ሌሊቱ-አብሮ ዶልቶብኝ
የእናቴን ገጽታ-አባቴን ምስሉን
ክዋክብትን ሳላይ- ጠፈሩን ሰማዩን
ባህርና ሃይቁን- ጋራ ተራራውን
ኒያላ ዋልያ -ፍንጠዛ እምቦሳውን
የቆንጆን ፈገግታ-የዓይኗ ነፀብራቁን
የጀግና ፉከራ- ፈሪ መርበትበቱን
አዛን አላየሁም-ጸሎትና ድዋ
ቁራን አላነበብኩ- ወንጌል ጾመ ድጓ
ጨረቃን ሳላውቃት-ፀሃይን ሳልሞቃት
ዓለምን እንደ ዓለም-ፈፅሞ ሳላውቃት
ግርም ሳይለኝ- ዓይኔ ሁሉን ዓይቶ
የማየት ምንነት-ከእኔነቴ ጠፍቶ
ይኸው እኖራለሁ-እድል እንደሰጠኝ
ማየት የሚሉትን-አላግባቡ ነፍጎኝ፡፡
አውቃለሁ አምናለሁ- ክርክር አልገባ
አልሞክርም እኔ- የለ እሰጥ አገባ
እድል እኔን ብቻ- ማየት አልነፈገ
አድልዎ እየፈፀመ-ልብን እያዛገ
ህሊናን በምኞት-ዘልቆ እያማለለ
አካልን በጽኑ-ልብ እያቆሰለ
ትናንትም ነበረ- ይኸው ዛሬም አለ
የእኔማ እሮሮዬ- ሃዘኔ ለቅሶዬ
ደስ ባይለኝ ነው-በዛሬ መሪዬ፡፡

ሆሜርን ከግሪክ-ሳምሶንን ከእስራኤል
የአላባማዋ እምቡጥ- ውቧን ሄለን ኬለር
አንድ ያደረጋቸው- ያመሳሰላቸው
ሰው መሆናቸው ነው- ብዬ እንዳልላቸው
ከመንጋው ካሉበት-ከተደበቁብት
ነጥረው ተስፈንጥረው-ጎልተው የታዩበት
ልዩ ምልክቱን-ሚስጥሩን ሳጤነው
ጥሩ መሪ ማግኘት-ሆኖ ነው እማገኘው።
ሆሜር ጥሩ ገጥሟል- ግሪክ ጠጅ ጥሎ
ሄለን ቀጭን ፈታይ- ብዕረ አመልማሎ
ሳምሶን ግዳይ ጣለ-አዕማዱን ታግሎ
ህሊና አይና አወጣ- ልብ በር ከፈተ
አይነስውር ጃሎ-ጀግና ድልን ሻተ
ወንዱ ደም መለሰ-ጠላት ተከተተ።

የአላባማ ፀሃይ-የአሜሪካ አበቦች
የእስራኤል ኮረዶች-የግሪክ ፀዳሎች
ፍጡረ ሥላሴ- ወይም አማልክቶች
ሁሉም በዚህ ምድር-የሚርመሰመሰው
በላይኛው ሰማይ-በአክናፍ የሚከንፈው
በህዋው በጠፈር-ተንጣሎ እሚታየው
ውበቱ ቢገለጥ-በሄለን በሆሜር
የሰሙትን እንጅ-ያዩትን አልነበር
ክታቡና አክታቡ-ስንኝ ቢደረደር
ልብም ሃሴት ቢያደርግ-ህሊና ቢዘምር
ሚስጥሩ ቢደንቀን-ያስረከቡን ነገር
ይሄ ከየት መጣ-ቢለው ቢጠይቁ
የእውቀቱን መስመር-መምጫውን እንዲያውቁ
ሃሳብ ተፀንሶ-ተወልዶም ያየነው
መሪው ለመምራቱ-ብቁ ሆነና ነው።
እኔም አይነስውር- የዛሬው ሆሜር
ሳምሶን ነኝ እኔማ -ወንድመ ኬለር
ጉዞዬ አስቸጋሪ- ከመሆን በቀር
እመዘገብ ነበር- በታሪ መዝገብ
መሪዬ ባይጨክን-ክፋት ባያስብ።
እናንተ ወገኖቸ-የአጥንቴ ፍላጮች
አዛኝ እህቶቸ-ልበ ደጋ ደጎች
መሪዬን ተኩልኝ-በሉ አስወግዱልኝ
የዛሬ ኑሮየን-አያበላሽብኝ
የነገ ተስፋዬን- አያጨልምብኝ።

ዳግማዊ ዳዊት
ነሐሴ 2001 ዓ.ም.
ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: