Tuesday, August 25, 2009

እርጉዟ ሚስቴ

ዳግማዊ ዳዊት

ቀረ አልቀረ ሚስቴ- በዚህ ወር አርግዛ
አማረኝ ትላለች- ፍትህ እንደዋዛ
ጠዋት ከእንቅልፍ ነቅታ- ምሬት ምሬት ሲላት
ምግብ አይበላት- ውሃም አይጠጣት
ምን ላቅርብ ምን ላምጣ- ብዬ ስጠይቃት
አንድነት ትላለች- ነጻነት በፍትህ
ብቻየን አልጥድህ- ፍትህ ከየት ላግኝህ?
“ሙያ ዱሮ ቀረ” ትለኛለች አዝና
ጠይቃኝ ሳላገኝ- ፍትህ እንደገና
“ያኔ ዱሮ ዱሮ- አባቴ ተረግዘው
እማሆይ አያቴ- ፉከራ ሲያምራቸው
ዘራፍ ሲሉ አባባ- የአባ ዳኘው አሽከር
ግርማው የአባ በዝብዝ - ሙያው ያምር ነበር
አንተማ የኔ ባል- ባሌ የተባልከው
ፍፁም አላየኸው- ሙያውን አታውቀው
ዘራፍ አትል አንተ- ፍጹም አልዋልክበት
እኔ ባለሁበት -አንተ እየኖርክበት
ማን ይበል ይፎክር- ዘራፍ ይበል ወንዱ
አብረን መዋላችን- አይደልወይ ገሃዱ
ትናንት ጀምሬ- ጠይቄ እርጉዝ ሚስትህ
አማረኝ እያልኩህ- ነጻነት በፍትህ
ሙያ በአንተ የለም- ባንተስ ወንድነትህ”
ብላ ወንድነቴን- ፈተና ከታው
ጉድ ሆኛለሁ ዛሬ- እንዴት ልወጣው?
እኔ ደካማው ባል -ጀግንነት የሌለኝ
ሚስቴ ያማራትን- ማቅረቡ ተሳነኝ።
የትናንት ጀግንነት- የአባቶች ወንድነት
መተባበር ነበር- መታገል በአንድነት
ዛሬ የኔ ትውልድ- አንድነት አቅሮት
ኑሮውን ይገፋል-በሃዘን በምሬት።
ማቅረብ እኔ እንድችል- ሚስቴ ያማራትን
ከሁላችን በፊት- ትቅደም ሃገራችን
ፍፁም አይጠቅመንም-መለያየታችን
እስኪ ሁላችንም- እኛኑ እንይና
ምን እንደሚጎለን-እንመርምርና
እንታገል ትግልን- አንድ እንሁንና።

ዳግማዊ ዳዊት
ethio_dagmawi@yahoo.com
ነሐሴ 2001

No comments: