Monday, January 25, 2010

እያንጓለለ! (የምርጫ ጭውውት)

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ሊቀ መኳስ ቆመ- አራት ኪሎ ላይ
ትናንት መለስ መለስ…
ዛሬም መለስ መለስ…
ነገም መለስ መለስ- መለስ መለስ ባይ።

አገር አሳደጉ
ሰላም አወረዱ
ይህን አድርገዋል -ስሙ ያልሰማችሁ
ተገቢ ነውና-በሙሉ ድምጻችሁ
ለዘንድሮው ምርጫ-እነርሱን ባትመርጡ
ትዝብት ነው እንጅ-ምንም አታመጡ።

ኩኩሉ አለ ዶሮ
የምን ምርጫ ነው ዘንድሮ
ውጤቱን ያወቅነው ገና ዱሮ
መለስ ሊመረጥ ዞሮ ዞሮ!

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

መሪው ሊቀ መኳስ-አጭር ሰው መላጣ
“ላሌ ላሌ” እያለ- ይኸውና መጣ።

“ቂ! ቂ!....
ልደቱ ልደቱ- እያሉ ሲያለቅሱ
እነኃይሉም መጡ- ከእኔ ሊቋደሱ”

ኩኩሉ አለ ዶሮ
ማን ነው የሚገደል ዘንድሮ
ማን ነው አስገዳይ ዘንድሮ

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዝ ልደቱ…

አውቄ ነው እንጅ ድሮም ስግደረደር
እኔስ ለአድዋው ሰው-አሽከር ሆኘ ልደር
እንደምን ነው ስሜን-ወገብ ለወገቡ
እንደምን ነው ትግራይ-ወገብ ለወገቡ
የእነአዜብዬ አገር- የእነአይጠገቡ
አላማጣ ውዬ- መልሸ አላማጣ
ሽህ ሰው ይተላለቅ- እናንተን ከማጣ
እኔስ በመለስ ላይ- ክፉም አላመጣ።

ኩኩሉ አለ ዶሮ
ምን ተደግሶልናል ዘንድሮ

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዝ መለስ..

ብለነው ብለነው- የተውነውን ነገር
አምና ኃይሉ ስምቶ- ታንቆ ሊሞት ነበር
ዘንድሮ መምጣቱ- መስማማቱ ላይቀር
ልደቱን መውቀሱ- ተገቢም አልነበር።

አገራችን ትግራይ- ወንዛችን ተከዜ
ማነው እምቢ የሚል- ምርጫ ባልን ጊዜ።

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ኩኩሉ አለ ዶሮ
ኃይሉስ ምን አለ ዘንድሮ

በእስር በእንግልቴ- ሁሉ እማስብሽ
እኔም ልመጣ ነው ፓርላማ እንዴት ነሽ?
ኤልያስ የሚሉት-የሻዕቢያ ምላስ
መለስ ጠላት ብሎ-ሕዝብን ሲቀስቅስ
እኔም ወንድነቴ-ነሸጥ አድርጎኝ
ፓርላማ መግባቴ-ውርደት ነው አልኩኝ
ያ ክፉ ባለጌ- አሳሳተኝና
ባለፈው ባልመጣ- ባላይሽ ታችሃምና
ዘንድሮ ቁርጥ ነው-እንገናኛለን
እንዲህ ተለያይተን -መች እንቀራለን
መልክ ሰጠኝ እንጅ- ሲሉ እስማ ነበር
ሙያ ከልደቱ- ይኸው ጀመርኩ መማር።

እኔም ላሞግሰው-ልነሳ አደግድጌ
የአድዋው ሰውዬ- ባይሆን አብሮ አደጌ
አክብሮ ጥሪዬን- እጀን ሲጨብጠኝ
ከእራሴ ጀምሮ-ወገቤን ነዘረኝ::

ደጋፊ አስፈልጎኝ- በጋሪ ስገፋ
መለስን ስጨብጥ- በሽታዬ ጠፋ::

ይኸው መፎከሬ- “መለስ ይውረድ” ቀርቶ
ሰላም ሰላም ሆኗል- የዘንድሮው motto::

እኔ ፍራሽ ሆኘ- ልደቱ ትራስ
እንጠብቃለን- አልጋህ እንዳይፈርስ።

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ኩኩሉ አለ ዶሮ
በየነስ ምን አለ ዘንድሮ

ዓመት አስር ዓመት- የደነስኩብሽ
አንች ዉቧ ቆንጆ- ፓርላማ እንዴት ነሽ
ህዝቡ ቢቃወመኝ- አትግባ ቢለኝም
እመኝኝ ፓርላማ- ከአንች አልለያይም::

ዘጠና ሰባትን- ጠፍቶ እሚገድብ
ቅንጅት ተፈጥሮ -ወጣና ከህዝብ
ለጥቂት ተረፍኩኝ- ዱላ ከሚመዝ
ዳግመኛ እንዳይመጣ- ያን መሳይ መዘዝ።

ወያኔ ስትዳር- ጎጆ ስትቀልስ
ያን ጊዜ ጀምሮ-እስካሁን ድረስ
ታማኝ ተቃዋሚ-ሆኘ ለመለስ
መልካም ተብሎ ለእኔ- ህዝብም ተዘናግቶ
ያልፈኛል ሁልጊዜ- እንዳላዬኝ አይቶ።

ኩኩሉ አለ ዶሮ
ምን መዓት ይመጣል ዘንድሮ

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዝ ኃይሉ…

አድዋ ላይ ሆኖ- መለስ ቢደነፋ
ብርሃኑ ነጋ- አገር ጥሎ ጠፋ
ድሮም በእጀ- ያልኩት መስፍንን አምኘ
ያኔ እርሱን ማመኔም- ፍፁም የዋህ ሆኘ
“በብልቃጥ ተረግዞ- መስታወት ተወልዶ”
ድርጀት መባሉም- ወይ ነዶ ወይ ነዶ
እንግዲህስ በቃኝ- መስፍን የለ ሌላ
ጠቃሚ ላይሆኑ- የኋላ የኋላ
ፓርላማው ሰፊ ነው- ቧ ያለው መንገዱ
ስነ ምግባር ብቻ መፈረም ነው ኮዱ።

ቀብቸ አሽሞንሙኘ- ከላይ ባረግሽ
አምባ ገነን ብለሽ- ስሜን አጠፋሽ
በገዛ ምላሷ- በገዛ አንደበቷ
ቃሊቲ ገብታለች- ከዘላለም ቤቷ
አትሳቂ እያልኳት- ባህር ማዶ ስቃ
አመጣችው እስሩን- ነቅንቃ ነቅንቃ።

ኩኩሉ አለ ዶሮ
በችግር ላይ ችግር ሆኖ የእኛ ኑሮ

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዝ ብርሃኑ…

ስሙልኝ ይኸን ሰው- እዩት ስም ሲያጠፋ
ምርጫ ውሸት ነው ብል-አለኝ ጥሎ ጠፋ
እኔስ ያከበርኩህ- በሽምግልናህ ነው
አመራር ሲመጣ- ጉድክን ሳስተውለው
አምባገነንነት- ፍጹም መለያህ ነው

እነ መለስ ዜና -ሰይጣን መርቋቸው
ተቃዋሚ ጀባ- ብለው በጫታቸው
አንገዋለለና-ልደቱን ሰጣቸው
አንገዋለለና- በየነን ሰጣቸው
አንተን በምራቂ- ይኸው ጨመራችው

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዥ ብርቱካን…

ዓለም ዓለም…ዓለም ዓለምዬ
እሽሩሩ ስቃይ- ውረድ ከጀርባዬ
ደብተራው የማነ-- አረጋሽ እህቴ
አብረው የሚኖሩ- ቤታቸው ከቤቴ
የእግዜር ፈቃድ ሆኖ- ቢሰማ ጸሎቴ
ለፍች ያብቃችሁ- ከአላማችሁ ግብ
አምላክ ያውርድና- የሰላም ድባብ።

ዛሬ በመልዓኩ- በገብርኤል በበዓሉ
ወዲ መለስ ዜና- መሽረብ ጀመረ አሉ
ኃይሉ መላጣ ላይ- ሽሩባ ጎንጉኖ
“እኔን እኔን ስራኝ” ይላል ልደት አብሮ
ጸጉር እንዲህ ይሰራል- ከክዳን ጀምሮ።

ተወኝ አላልኩም ወይ- ይህን ዓመልህን
ልክ እንደልደቱ- አንተም መክዳትህን
ልደቱስ ቢያንስ እንኳን- ይሄድ ይመለሳል
ምርጫ መጣ ሲሉት- መለስን ይወቅሳል።

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

*********
ኩኩሉ አለ ዶሮ
አራት ኪሎ አስመራን ምን ይላል ዘንድሮ

ያዝ መለስ…

ከሰማዩ በላይ- ያለኸው ሰማይ
ወዲ አፎም በጤናው- ዘግቶኝ ቀረ ወይ
ደግሞ በዚህ ምርጫ ያደናቅፍ ወይ?
የቀይ ዳማ ረጅም- ጎራዴ ታጣቂ
ልግደልህ እያለኝ- እኔ እርሱን ናፋቂ

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ኩኩሉ አለ ዶሮ
ኢሳያስ ምን ይላል ዘንድሮ

ልቤ አብጦ ጀግኘ- አንበሳ ነኝ ስል
ጦር አዘመትክና- አደረከኝ ድል
አስራ ሁለት ሌሊት- አስራ ሁለት ቀን
ከትግራይ ተነስትህ- ልትይዝ አስመራን
ጉዴ ፈልቶ ነበር- ክሊንተን ባይኖር

ያስጎራሃል አሉ- በየአምስት ዓመት
ደም የለመደ እጅህ- ሲሻ መስዋዕት
ሲሉ ሰምታ ሆኖ- ሆነና ነገሩ
ምዕራብ ያለው ሁሉ- ይመስልሃል ጥሩ።

ምርጫ ምርጫ-ብለህ ብትፈጥር ግርግር
እኔ ጌታህ ሆኘ- ካልሆንከኝ አሽከር
ውጊያ መቀስቀሱ- ምንጊዜም አይቀር።

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዝ መለስ

ጠያቂው ቢያስጨንቀኝ- ስለኤርትራ ሁኔታ
አልወዳትም አልኳቸው- እንዲያገኙ ፋታ።
ቁርጡማ ሲመጣ- አስመራ ልትያዝ
የኔ ተግባር ነበር- እነስየን ማዘዝ
አልጀርስ ሳገኝህ- ውል ልትፈራርም
አልንበረምና- እኔ ያልኩኝ ጥምጥም
ይናፍቃል ላካስ- እንደዚያ ዎንድም።

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ያዝ ስዬ…
ተወኝ አላልኩም ወይ- ይህን አመልህን
ጫት እንዳዬ ጀዝባ- አስመራን መዞርክን
ጫትን ያዬ ቃሚስ- ቅሞ ይመለሳል
የአንተ ሁኔታ ግን- ግራ ነው እሚያጋባን።

እያንጓለለ!
ያ ገብስማ ዶሮ- ዘንድሮስ ምን አለ?

ኩኩሉ አለ ዶሮ
ህዝባችን ምን አለ ዘንድሮ

የሚመጣው ምርጫ- ምኞታችሁ መክኖ
የፍትህ አካላት- ፕሬስ ነጻ ሆኖ
ገለልተኛ ሆኖ- መከላከያችን
ገለልተኛ ሆኖ- የምርጫ ቦርዳችን
በነጻ እንዲስማ- እንደ ህዝብ ድምጻችን
በዘር በሃይማኖት- መጋጨት ትታችሁ
ኤርትራና ትግራይ
አማራ ኦሮሞ ማለቱን ትታችሁ
አብዮት-- አብዮት ማለት አቁማችሁ
ሁላችንን በእኩል- ሕጉ እንዲመዝነን
የስልጣኑ ምንጮች- እኛ ህዝቡ እንሁን።

ዳግማዊ ዳዊት
ጥር 2002

No comments: