በዳግማዊ ዳዊት
ጥቅምት 2002
Ethio_dagmawi@yahoo.com
“ሕዝባችን ተስብሰብ-ለሰበሩ ዜና
ባለጸጋው ጻድቅ- መሆኑ ይሰማ
ይኸ ባለጸጋ- ይኸ ያገሬ ሰው
ይኸ ባለሆቴል- ይኸ ወርቅ አንጣሪው
የሥራ ዕድል ፈጥሮ- ልቤን አስደሰተው”
ብሎ ጋዜጠኛው -ፅፎ አነበብኩና
ስለዚህ ባለሃብት- ሃሴት አረግሁና
እኔም የበኩሌን-ለገስኩት ምስጋና
“አንደበት ይከፈት-ጆሮወች ያዳምጡ
ለዚህ ባላፀጋ- ሽልማቶች ይምጡ
በል እግዜሩም ስማ- ፅድቅ ተለውጧል
ከዛሬ መነኩሴ- ባላፀጋ በልጧል
“ፀሃይ ትቁምለት- ትዘግይ ጨረቃ
ይኸ ባለፀጋ- እስኪል ድረስ በቃ
እስከሚበዛለት -ሃብቱ እስከሚስፋፋ
ሌሊቱም ቀን ይሁን -ብርሃን አይጥፋ።”
ብዬ ምስጋናየን- ሳዥጎደጉደው
ይኸ የአጎቴ ልጅ-የተበሳጨው
ከእኔ የተለየ-ሚስጥር ያውቅ ኖሮ
እንዲህ ሲል ነገረኝ-ሃሳቡን ቀምሮ።
“ለተራበ ማብላት-ለታረዘ ማልበስ
ታማሚ ማጽናናት-ለችግርም መድረስ
መጾም መፀለዩ-ቅንነት ማሰቡ
መች ሆኖ ተገኘ- የዛሬ ሰው ግቡ!
“ከደሃ ቀምቶ- ከደካማ ዘርፎ
ቢኖርም ቢሞላም- ተርፎ ተትረፍርፎ
ወርቅና አልማዝ ይዞ- ነዳጅ አስቆፍሮ
ሆኖ መገኘት ነው-ካለመጠን ከብሮ
ሰውን ሰው ያሰኘው- የለየው ዘንድሮ።
“የስው ልጅ ሲፈጠር- በጌታዬ አምሳያ
ነበረ ለታላቅ- ለክብር ማሳያ
ዛሬ የስው ልጆች- ወረቀትን ፈጥረው
ቁጥር ጽፈውበት- አንድ ሁለት ብለው
አረንጓዴ ቀለም- ቅርጻ ቅርጹን ስለው
ከራሳቸው በላይ- ለብር ክብር ሰጥተው
መኖር ጀምረዋል-ከሱ በታች ሆነው።
…
“መልኩን ሳፈላልግ- ጠይም ወይም ቀዩን
ቀረና የእርሱነት- መምሰል አምሳያውን
ንዋየ ፀሎቱ- ገንዘብ ሆኖ አምላኩ
አረንጓዴ ሆኗል- ባለጸጋው መልኩ።
…
“አንተን መሳይ ሰወች- እናንት ኋላ ቀሮች
ጠይምና ጥቁር-ቀይ አመላካቾች
ልታውቁ ይገባል- የዛሬን እውነታ
በጠይም በጥቁር- በቀይ ሰው ፋንታ
የሰው ልጅ ውበቱ- የሚያምር ቁመናው
አረንጓዴ ሆኗል- የእርሱ ሁለመናው።
“ገንዘቡ ዳኛ ነው- ፖሊስም ጠበቃ
ሃይሉ ልክ የሌለው- ተቆጥሮ አያበቃ
ፍትህና ክብር -ገዥ በገንዘቡ
ይኸ ባለጸጋ- ባለ ወርቅ ቅቡ
ሕጻን ሴት ያገባው- ሕፃን እቁባቱ
የስው ሚስት የቀማው- አድርጎት መብቱ
ሁሉ ሰው ጌታዬ- ብሎ የሚጠራው
እርሱን ነው የሚያደንቅ- ጋሸ ጋዜጠኛው።
ብሎ ተናገረ- ይኸ የአጎቴ ልጅ
ስለ አረንጓዴው ሰው- ለሁሉ እንደማይበጅ።
ትናንት ህጻን ሆኘ-ሳድግ በሰፈሬ
የሰው ልጅ መጠሪያው- ልዩ ነው ከዛሬ
አይደለ በልብሱ- በፀጋ በሃብቱ
አይደል በቁመናው- ተክለ-ሰውነቱ
አይደል በትምህርቱ- በዕውቀት ሊቅነቱ
ሰው በሰውነቱ- ሲለካ የማውቀው
ፍጹም ልዩ ነበር- ዛሬ ከምናየው።
አንገቱን ለፍትህ- አንደበቱ ለእውነት
ውሸትን የጠላ- ግፍን የሚጋፈጥ
ከክፎወች ሸንጎ- ፈጽሞ የራቀ
አንቱ የተባለ-በአገር የታወቀ
ነበር የሰው መልኩ-ለእውነት መቆሙ
ትናንት የምናውቀው- የሰው ልጅ መልካሙ
ዛሬ ተለየና -ውበት ተቀይሮ
ዓይናችን የሚያየው- ብር ሆነ ዘንድሮ።
እስኪመለስ ድረስ -አይንም ወደ ድሮው
ስንናፍቅ ከዋልን- ገንዘብን እንደሰው
እውነትም ይዛባል-ፍትህ ይሰወራል
ገንዘብ የአገር ዳኛ- ጠበቃ ይሆናል
…
አንተ ጋዜጠኛ- አንተ ወሬ አቀባይ
እስኪ እንደ አጎቴ ልጅ-አንተም እውነቱን እይ
ያ ባለጸጋ ሰው- በዓለም የከበረ
እውነቱን አሰማን- ማን እንደነበረ?
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment