ትብብር፣ ሕብረት፣ ግንባር፣ ቅንጅት፣ መድረክ፣ አሁን ደግሞ ጥምረት
ልጅ ተክሌ (ቫንኩቨር-ካናዳ)
አንዱ ይሄ ቀጥዬ የምተቸው ክስተት የማይጥመው ወዳጄ፡ “ትብብር መጣ፡ ሕብረት መጣ፡ ቅንጅትም መጣ፡ መድረክም መጣ፡ እነሆ አሁን ደግሞ ጥምረት መጣ፡ እንግዲህ የቀረው ድብልቅ” ነው ብሎ ተሳለቋል። ከዛሬ ነገ አስመራ ገብቶ የግዞት መንግስተ ያቋቁማል ወይም አንዱን የሕወሀት ሚኒስትር አፍንጫውን ይለውና አንጀታችንን ያርሳል፤ እንደው ሌላው ቢቀር ባለበት ሆኖ በድፍረት እኛ ነን እንጂ እናንተ መንግስተ ልትሆኑ አይገባችሁም ብሎ ይናገራል ብዬ ስጠብቅ በዚህ ጊዜ አለን የምንለው ጠንካራው የፖለቲካ ድርጅት ግንቦት ሰባት፣ አንዱን ግንባር ወይም ትብብር በቅጡ ሳናጣጥም ሌላ ጥምረት የሚባል ፍጥረት ይዞ ሲድህብን በጣም ተበሳጭቻለሁ። እኔ ጸረ-ፓርቲዎች-ጥምረት ነኝ። የስራ እንጂ የፕሮግራም ትብብር አይመቸኝም።
የተግባር እንጂ የአመራሮች ህብረት አይጥመኝም። ጠላታችን ሕወሀትም ይሁን ወዳጃችን ሻእቢያ ያሸነፉን በማጥቃት ጥምረት ነው እንጂ በፕሮግራም ትብብር አይደለም ባይ ነኝ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ነሀሴ 20/2002 የወጣ አንድ መግለጫና ዜና፤ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነትና የፍትህ ንቅናቄ ተቀናጅተው “ጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያን” መስርተዋል ሲል ይናገራል።[1] መግለጫው የዚህን ጥምረት መፈጠር እንደዜናም እንደምስራች ያስቀምጠዋል። እኔ ግን ይሄ የምስራችነት የሌለው እንዲያውም ያው የተለመደውን የምንጠቃበትን ፖለቲካዊ አካሄድ የደገመና ፋይዳ ቢስ ፖለቲካዊ ርምጃ ነው ባይ ነኝ። ይሄ የጥምረት ምስረታ እዚህ ላይ ሳያቆም፤ ድርጅቶች አቅማቸውንና ጥረታቸውን አስተባብረው ቢሰሩ ወያኔን ለመጣል ስለሚረዳ ሁሉን አቀፍ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረት ለማምጣት ይተጋሉ፤ ይሄም በግንቦት ሰባትና አጋሮቹ የተመሰረተው ጥምረት የዚያ ሁሉን አቀፍ ሕብረት የመመስረት እንቅስቃሴ መጀመሪያ ነው ይላል መግለጫው። ገና ሌላ ሕብረት፣ ሌላ ጥምረት፣ ሌላ ግንባር ይመጣል ማለት ነው። ትግሉ መንገድ ጠራጊ መጥምቁ ዮሃንስን መላክ ብቻ ሆነኮ ጎበዝ። ክርስቶስ አልመጣ አለን።
ሕብረት፣ ጥምረት፣ ክስረት ናቸው፡ የእብደት ስራዎች፦
እኔ የምለው ብዙ ነገር ቢሆንም አንዱ ግን ይህ ነው። ሰፊና ሁሉን አቀፍ ህብረት መመስረትና ማምጣት ወያኔን ከመጣልና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከመመስረት ጋር ምንም አያገናኘውም። እንዲያውም ከልምድ እንዳየነው ወያኔን ለመጣል ብቻ በግድ የሚመጣ ህብረትና ግንባር መጨረሻው ተስፋ በሚያስቆርጥና እንደገና ለመጣመር በሚያስቸግር መልኩ መፈረካከስ ነው ባይ ነኝ። እኔ ምን ሩቅ ወሰደኝ በኢትዮጵያ 18 አመት ታሪክ ውስጥ እንደ ህብረት፣ ጥምረት፣ ግንባር፣ ትብብር፣ ቅንጅት መፍጠር የሰለቸንና ትግላችንን የጎዳ ፖለቲካዊ ሙከራ የለም። ፖለቲካዊ ሙከራ ጥሩ ነው። ሰው ግን አንድን ነገር ሁልግዜ ሲሞክር አይኖርም። ሲሞክር አይሞትም።
እብደት ማለት አንድን ነገር በተመሳሳይ መልኩ ደጋግሞ መሞከርና የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው ከተባለ ግንቦት ሰባትም ይሁን ሌሎቹ ድርጅቶች የሰሩት ጥምረት የመፍጠር ስራ የእብደት ስራ ነው። ተሞክሮ ተሞክሮ ያልሰራን ነገር ነው በዚያው በፊት በተሞከረበት መልኩ ነው የሚሞክሩት። ምንም አይነት የፖለቲካዊ ንጥረ ነገርም ይሁን የፖለቲካዊ ቀመር ለውጥ የለውም። በፊትም የተደረገው እከሌ እንቶኔና እከሊት የተባሉት ድርጅቶች ወያኔን በጋራ ለመጣል ሕብረት መሰረቱ ነው። አሁንም ያው ነው። ለውጡ የስም ብቻ ነው። ይሄ እንደ ትልቅ የምስራች ሊነግሩን የሚገባ ዜና አይደለም ባይ ነኝ። ላንዳንዶቻችን እንዲያውም ይሄ መርዶ አይነት ነገር ነው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በሚፈጠሩ ትብብሮች ውስጥ ያየነው ተሞክሮ አንድም መፍረስ ሌላም የትም አለመድረስ ነውና፤ ደግሞ እንደገና ስንሳቀቅ ከምንኖር ባንሰማው ይሻል ነበር።
ጥምረትና ህብረትን የምጠላባቸው ምክንያቶች፡ አጉል ፉክክር ይፈጥራሉ
አንደኛ ነገር እንዲህ ያሉ ትብብሮች ወይንም ቅንጅቶች ጤናማ ላልሆነ ፉክክርና ፖለቲካዊ ሽኩቻ በር ይከፍታሉ። በድርጅቶቹ መካከል የተዛባ የሰው ሀይል፣ የአባላት ቁጥር እና የሀብት ስርጭት አለ። ያንን አስተናግዶና አቻችሎ መጓዝ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሄ ጥምረት፣ ህብረት፣ ትብብር ምናምን የሚባል ነገር እኛ ልጆች ሆነን በምንመኘው የየዋሀን ምኞትና መተማመን የተጎነጎነ የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ፖለቲካ ውስጥ ውድድርና ፉክክር አለ። አንዱ ይበልጣል አንዱ ደግሞ ያንሳል። በአናሳዎችና በሀያላን መካከል የሚደረግ ሕብረት ወይም ጥምረት ሀያላኑ ዘወትር ስለስራቸው ሳይሆን እንዴት አድርገን አናሳዎቹን እናስደስት በሚል ደካማዎቹ ደግሞ እንዴት አድርገው ሀያላኑ ጥቅማችንን ጎዱ ወይም ጠቀሙ በሚል ጥያቄ የሚጠመዱበት ሂደት ነው። ይሄ ጥምረት አጉል ፉክክርና አጉል ሽኩቻ ይፈጥራል። ፖለቲካችን የራሱ በቂ ሽኩቻ እያለው እነዚህ ድርጅቶች እንደገና ጥምረት የሚባል ነገር ፈብርከው ሌላ ሽኩቻ ማከል አልነበረባቸውም።
ሕብረት የመፍጠር ትግል እንደ ግብ
ሁለተኛ ይሄ ህብረት፣ ትብብር፣ ግንባር፣ ቅንጅትን የምጠላበት ምክንያት እነዚህ ትብብሮች ወደግብ መድረሻ መንገድ ሆነው ሳለ በራሳቸው እንደ ግብ ወይም እንደ ስራ እየተወሰዱና በርግጥም ስራ ለመስሪያ መስሪያ ሳይሆኑ ድክመትን ለመሸፈኛ ዘዴ እየሆኑ ስለመጡ ነው። ግንቦት ሰባትን ወይንም በዚህ ጥምረት ውስጥ የተሰለፉትን ድርጅቶች ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን ብዙ ድርጅቶች የተቋቋሙለትን ስራ መስራት ሲሳናቸው፡ ህብረት መፍጠርን እንደ ስራ ያዩትና ህብረት ወይንም ግንባር ወይንም ትብብር ፈጠርን ብለው እንደ ተጨማሪ ጥቂት ወራት ማግኛ ወይንም ግዜ መግዣ የሚጠቀሙበት የፖለቲካ ግርግር ሆኖብኛል። ግንቦት ሰባት ከተቋቋመ ግዜ አንስቶ ብዙ ስራዎችን ለመስራት የሚሞክርና የሰራ ድርጅት ቢሆንም፡ ከዚህ ከላይኛው ክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ ሊሆን ግን አይችልም።
ቀድሞውንስ ሶስት አራት ለመሆን ምን ምክንያት አለን?
ሶስተኛው ምክንያቴ፡ ቀድሞውንም ነገር አንዳንድ ድርጅቶች የተለያዩ ድርጅት ለመሆን ምንም አይነት አጥጋቢ ምክንያት ሳይኖራቸው ብቻ በኩራት የቆሙ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ የአፋር ወይም የኦሮሞ ወይንም የሲዳማ ድርጅቶች የወጡበትን ብሄር ብቻ መሰረት ያደረገ ጥያቄና አጀንዳ ሊኖራቸው ይችላልና ሰማኒያ አምስት የብሄር ድርጅቶች ቢፈጠሩ አይገርመኝም። ነገር ግን በዚህ አሁን በተፈጠረው ጥምረት ብንሄድ፡ የግለሶበች ጸብና ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የተቀሩት ሁለት ድርጅቶች ህብረ-ብሄራዊ አጀንዳቸው ተመሳሳይና ብሄርን ሳይሆን ኢትዮጵያን መሰረት ያደረገ ፍላጎት ያላቸው ናቸው። አንዱ የኢትዮጵያ አንድነትና ፍትህ ንቅናቄ ነው። አንዱ ደግሞ የነጻነት፡ የፍትህና የነጻነት ንቅናቄ ነው። ስለዚህ የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር ከግንባር ወይም ጥምረት ይልቅ አጀንዳቸውን አስተካክለውና አስማምተው ውህደት የማይፈጽሙበትና እንደ አንድ ውህድ ድርጅት የማይቆሙበት ምክንያት ምንድር ነው? ምንም። የብሄር ድርጅቶቹን እንተዋቸውና፡ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ነአምን ዘለቀን ከዶ/ር ብርሀኑ ምንም የሚለየው መሰረታዊ ነገር ስለሌለው ሁለት ድርጅት አያስፈልጋቸውም። ሁለቱም ባንድ ድርጅት ታቅፈው መንቀሳቀስ እየቻሉ፡ የምንታገለው ለኢትዮጵያ አንድነት ነው እያሉ እንደገና ደግሞ ሁለት ሶስት ድርጅት ውስጥ ሙጭጭ ብሎ ጥምረት፣ ትኩረት፣ ምናምን እያልን ጊዜና ጉልበት የምናባክንበት ምክንያት አይታየኝም።
ስጋቴ ምንድን ነው? በፍትወት የሚቃጠል መነኩሴ አይነት ነገር
ስጋቴ እንደሚከተለው ነው ትብብር ማለት ሁሉም የራሱን የድርጅት ፍቅር ሳይገድል፣ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ይዞ የሚመጣበት፤ በኋላ በጋራ ከሚሰራው ስራ በይበልጥ የራሱን የድርጅት ጥቅም አስቀድሞ እኔ ምን አገኛለሁ የሚለውን ነገር የሚያስብበት አወቃቀር ነው። ለዚህ ከቅንጅት የተሻለ ተሞክሮና ከዶ/ር ብርሀኑ የተሻለ ምስክር የለም። እሱ ራሱ በጻፈው የነጻነት ጎህ ሲቀድ በተሰኘ መጽሀፉ ቅንጅትን ለመፍጠር ከተፈጠረም በኋላ ቅንጅትን ለመጠበቅ የነበረውን መከራና ፈተና አሳይቶናል። ትብብር፣ ቅንጅት፣ ግንባር፣ ህብረት ምናምን የሚባሉ ነገሮች የወሲብ ስሜቱን ሳይገድል እንደሚመንኮስና በኋላ በፍትወት እንደሚቃጠል መነኩሴ ይመስሉኛል። ድርጅታዊ ፍትወታቸውን ይዘው ጥምረት ይመሰርታሉ፡ በሁዋላ በድርጅታዊ ፍትወታቸው ጥምረቱንና ትግሉን ያምሱታል።
ለነገሩ ወደታች በሰፊወ እወርድበታለሁ፤ እኔ የምለው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የፓርቲዎች ውህደት ከዚያ መለስ ደግሞ ሁሉም የራሱን ስራ ብቻ እንዲሰራና ርስ በርስ እንዳይጠቃቃ የሚይዝ ስምምነት ነው እንጂ ወራትና አመታት የሚፈጅ የድርጅቶች ጥምረት ወይንም ትብብር ምስረታ አይደለም። ድርጅቶች የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ፤ ወደ ውህደት ማምራት ነው ያለባቸው። የብዙሀን ፓርቲ ስርአትን መቃወሜ አይደለም ነገር ግን ድርጅቶች መዋሀድ ካልቻሉ፡ ሁለተኛ ማድረግ የሚችሉት ነገር፡ ሁሉም ድርጅት ስራዉን እንጂ የሌላውን ድርጅት ስራ እንዳይነቅፍ፣ ትኩረቱ የጋራ ጠላት ላይ እንጂ ርስ በርስ እንዳይሆን ብቻ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ እንጂ ጥምረት፣ ሕብረት፣ ትብብር ምናምን የሚባሉ ነገሮች ግርግር ለመፍጠርና ላንድ ቀን ዜና ፍጆታ ብቻ የሚውሉ ምንም አይነት ዘላቂ ፖለቲካዊ ፋይዳ የሌላቸው ፍጥረቶች ናቸው።
የግንቦት ሰባት ርእሰ አንቀጽ
ግንቦት ሰባት ድርጅት በሴፕቴመበር 3 ርእሰ አንቀጹ እንዳለው ይሄ ጥምረት “የተደራዳሪዎችን ቁጥር ከመቀነስ ውጪ” ምንም አይነት የላቀ ሚናና ፋይዳ አይኖረውም።[2] የግንቦት ሰባት ርእሰ አንቀጽ ከአሁን ቀደም ከተመሰረቱ ህብረቶች ዘላቂነት ማጣት አንጻር ከዚህ በኋላ የምንመሰርተው ህብረት ያለፉትን ስህተቶች የሚደግም መሆን የለበትም ይላል። ጥምረት የሚባል ነገር መፍጠሩና እንደትልቅ ድል ማብሰሩ በራሱ ትልቅ ስህተት መድገም ነው። አንደኛ ነገር ይህ ጥምረት ያለፉትን ህብረቶች ስራ ከመድገም ውጪ ያደረገው ወይም የሚያደርገው ምንም አይነት የተለየ ነገር ሊገለጥልኝ አልቻለም። ከዚህ በፊት የነበሩት ጥምረቶች ችግር ትኩረታቸው ዓላማቸውን እንዴት እናሳካዋለን የሚለው ነጥብ ላይ ሳይሆን እንዴት ስልጣን እንደላደል ነው። ማን ጸሀፊ፣ ማን ሊቀመንበር፣ ማን ምክትል ይሁን አይነት ነገር። በዚህ ጥምረት የስልጣን ድልድል ተደረገ። አንዱ ድርጅት ሊቀመንበር፣ አንዱ ደግሞ ምክትል፣ አንደኛው ደግሞ ጸሀፊ ሆነ። ከዚያ መለስ ሌላ ምንም ነገር የለም። በቃ የጥምረቱ ስራ እዚያ ጋር አበቃ። ከዚያ ፈቀቅ ሊል አይችልም። ቀጥሎ የምንሰማው አንዱ ድርጅት ሌላኛውን ድርጅት ሲከስ ነው።
ስላልን ብቻ የሚሳካ ነገር የለም፤ እንዲያውም ግርግር ይፈጥራል
ግንቦት ሰባት ወይም አሁን የተፈጠረው ጥምረት “ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ህብረቶች የነበረባቸውን ድክመት በማረም አሁን የሚፈጠረው ወይንም የተፈጠረው ህብረት ከሌሎቹ በተሳካ መልክ ይሰራል” ስላለ ብቻ የሚሳካ ነገር የለም። ጥምረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት፤ ተባባሪዎቹም ፖለቲከኞች ናቸው። ከዚህ በፊት ከነበሩት ጥምረቶች ምንም የተለየ የሚያደርገው ነገር የለም። ፖለቲከኞቹም ከዚህ በፊት ተሞክረው በነበሩ ትብብሮች ውስጥ በተለያዩ መልኩ ሰርተው የተሳካላቸውም ያልተሳካላቸውም ፖለቲከኞች ናቸው። ስለዚህ ያው የቀደሙትን የመተባባርና የመገነባበር ጥረት የሚደግም እንጂ የተለየ የሚያደርገው ነገር የለም። እንደውም የዚህ ጥምረት መምጣት ሌላ የሚፈጥረው ግርግር አለ። የስያሜዎች መብዛት በህዝቡ ውስጥ ግር መሰኘትንና ግራ መጋባትን ይፈጥራል። የዚህ ህብረት፣ የዚያ ግንባር፣ የዚህ ቅንጅት፣ የዚያ ትብብር፣ የዚህ መድረክ። አሁን ዝርዝሩም ሊጠፋን ነው። ጓደኛዬ እንዳለው ቀጥሎ ድብልቅልቅ ሊመጣ ነው።
ነጥቤን ረሳሁት፤ ስንተኛ ላይ ነበርኩ? የሚያስፈልገን ድፍረት ነው
ሰባተኛ ይሁን ስምንተኛ እንጃ ብቻ ጎበዝ እንዲያውም ጥምረት፡ ክስረት ነው። ጊዜና ገንዘብ ሰውም ይበላል። ልብ አድርጉ ሕወሀትን ለመጣል የተቃዋሚዎች ሕብረት ያስፈልጋል ካልን፡ ይሄንን ጥምረት ለመፍጠር ደግሞ ድርድሩ ከአንድ አመት በላይ ከፈጀ፡ ሁሉን አቀፍ ሕብረት ለማምጣት ደግሞ ስንት አመት እንደሚፈጅ አስቡት። ይሄ ጊዜ ማባከን ነው። ዝም ብሎ ስራን መስራት ይሻላል። ሁሉም እየሰራ እየሰራ እየበረታ ሲሄድ ድርጅቶች ራሳቸው እንቀላቀል ብለው ይመጣሉ። እንጂ በባዶ ሜዳ ጥምረት ለመፍጠር አንድ ወርቅ አመት ማባከን የፖለቲካ ቅንጦት ነው። አሁን ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሕብረት ለማምጣት ሌላ ሶስት አራት አመት የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ደግሞ ሌላ አምስት አመት። ይሄንን ሁሉ ጊዜ ኢትዮጵያና ኢህአዴግ ቁጭ ብለው ይጠብቁናል። ግንቦት ሰባት የሚበጀውን ያውቃል። ግን እንደኔ እንደኔ ዝም ብሎ ስራውን እየሰራ ሌሎቹም ስራቸውን እየሰሩ አንድ ቀን ያለላቸው እለት ቢዋሀዱ ይሻላቸው ነበር። ለነገሩ እኛ የሚያስፈልገን ጥምረት አይደለም፡ ድፍረት ነው።
ምሳሌ ዶ/ር ብርሀኑ እና ግንቦት ሰባት
ሌላ ምሳሌ አሁን ዶ/ር ብርሀኑ እንደምንድን ነው የሚናገረው? እንደ ግንቦት ሰባት መሪ? እንደ ጥምረቱ መሪ? ይሄ የጥምረቱ ሃሳብ ነው፤ ይሄ ደግሞ የግንቦት ሰባት እምነት ነው እያልን ስንታገል ልንኖር ነው። ለደጋፊዎቹና ለተከታዮቹ እንዲሁም ለተመልካቾቹ የቤት ስራ የሚያበዛ ጥምረት፡ ክስረት ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ስም የሚመሰረቱ ድርጅቶች የራሳቸውን ድርጅት ጥቅም ለማስጠበቅ የሚራኮቱበት ትብብር ከመፍጠር ይልቅ እንደምንም አላማቸውንና ፕሮገራማቸውን አፋጭተው አንድ ፕሮግራም ፈጥረው ውህደት የሚመሰርቱበት እድል ለመፍጠር ነው መታገል ያለብን። ከዚያ በሁዋላ እንደ አፋር ያሉትን በብሄር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶችን በጋራ መስራት በምንችልባቸው ሁኔታ ላይ የምር ማወያየት። ከዚያ በተረፈ ግን አሁን የአፋር፣ ከዚያ ደግሞ የኦሮሞ፡ የኦጋዴን የእከሌ የሚባሉትን ድርጅቶች የምናስገባቸው፤ ለይምሰልና ለታክቲክ ብቻ የድርጅትንና የትግልን መልክ ለማሳመር ይመስላል።
ግንቦት ሰባት ምን ነካው?
በሌላ አነጋገር እኮ፡ የግንቦት ሰባት አዝማሚያ፡ እኔ ጎዶሎ ነኝ፡ አጀንዳዬም የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ አይወክልም የማለት ፈራ ተባ የማለት ነገር ነው። ስለዚህም በጥምረት ስም ክስረት የመጋበዝ ያህል ነው ያየሁት አካሄዱን። ግንቦት ሰባት አጭር እድሜ ቢኖረውም ብዙ ሰዎችን በሙሉ ግዜ የሚያሰራና በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአለማችን የተለያዩዩ ክፍሎች ብዙ አባላትንና ደጋፊዎችን ማፍራት የቻለ ትልቅ ድርጅት ነው። በተቃራኒው ሌሎቹ ጥምረቱን የመሰረቱ ድርጅቶች በሰው ሀይል ብዛታቸውም ይሁን በሀብታቸው ብዛት አናሳ ይመስላሉ። አንዳንዶቹ መኖራቸውንም አናውቀውም ነበር። እንዲያውም መኖራቸውን ራሱ የሰማነው ጥምረት መሰረቱ ሲባል ነው። ያ ይሁን፡ ቢያንስ እነዚህ ድርጅቶች ለአባላቶቻቸው ነበሩላቸው። ዋናው ችግሬ ግን ይሄ ጥምረት በሚታወቁና በማይታወቁ ድርጅቶች ሲመሰረት፤ የሚታወቁት ድርጅቶች በስራቸው ሳይሆን በመሰረቱት ጥምረት ብቻ ከታወቁ በሁዋላ ጥምረቱ ለስራ ሲንቀሳቀስ ከዋንኛው የአገሪቱ ጉዳይ ይልቅ ሜካኒካል የሆኑ የስልጣንና የምክክር ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር ድርጅቶቹ ርስ በርሳቸው ፉክክር እንዲያደርጉና እንዲካሰሱ መንገድ ይፈጥራል የሚለው ነው። ከዚህ በሁዋላ እነዚህ በስራቸው ሳይሆን በጥምረቱ መመስረት ምክንያት ያወቅናቸው ድርጅቶች በዚህ ጥምረት መመስረት ምክንያት ምንም አይነት ችግር ለመፍጠር አቅም ያገኛሉ። ጥምረት በስራ ላይ ለውጥ ስለማምጣቱ ዋስትና የለንም ችግር ስለመፍጠሩ ግን ካለፈው ልምድ ተነስተን በርግጠኝነት መናገር እንችላለን።
ሌላ ምሳሌ፡ የቅንጅት ነገር
የቅንጅት ምስረታ አንዱ ችግር ውስጣዊና ልባዊ አለመሆኑ ነው። መዋሀድ የማይችሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በግድና ለምርጫ ሲባል ብቻ ተዋሀዱ ተባሉ። ስለዚህም ቀደም ሲል እንደ ድርጅት የነበራቸውን የግል አተካራና ፍትወት ሳይገድሉ ወደ ቅንጅትነት ሄዱ። ከነ ፍትወቱ እንደሚመለኩሰው መነኩሴ ነገር ማለት ነው። ከዚያ በሁዋላ የግልና የድርጅት ፍትወታቸውን መግደል አልቻሉም ነበርና ፓርቲ መሆን አልቻሉም ነበር። ፈረሱ። የህወሀት ተንኮልና አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀድሞውንም ቅንጅት በግድ የተሰባሰቡ ድርጅቶች ፍጥረት ነበርና ስራውን በድል ከማጠናቀቁ በፊት ለውድቀት በቃ። ሌላ ማን ነበር? ትብብር ለነጻነትና ለዴሞክራሲ የሚባል መጣ (ኤ.ኤፍ.ዲ)። የት እንደገባም አናውቀውም። መድረክ አገር ቤት አለ ገና አልለየለትም። ብርቱካን እስር ቤት ገባች፡ ድርጅቷ አንድነትም አንዴ እንደመድረክ አንዴ እንደ አንድነት እየተንገዳገደ ሳለ፡ እነሆ አሁን ደግሞ እዚህ ጥምረት የሚባል ሌላ ፖለቲካዊ ጣጣ መጣ።
ጥምረት አልገባኝም፤ ይልቅስ ተዋሀዱ
የሚያስፈልገን ውህደት ነው። ከዚያ መለስ ሁሉም ዝም ብሎ ስራውን ይስራ። በቃ ስራውን ብቻ። በሌላው ስራ ጣልቃ አይግባ። ስራው ራሱ ጥምረቱንም ውህደቱንም ያመጣዋል። በወያኔና ሻእቢያ መካከል ተፈጠረ የሚባል ጥምረት፣ ግንባር ምናምን የሚባል የፕሮግራም ትብብር አላስታውስም። የስራ ትብብር ነበር የነበረው። ያም ሻእቢያነቱን ጠብቆ፡ ይሄም ሕወሐትነቱን ጠብቆ ጠላታችን የሚሉትን ደርግን ያጠቁ ነበር። የስራ ውህደት ነበር። አንዱ ላንዱ ትጥቅና ስንቅ ያቀብላል። አንዱ ላንዱ ደጀን ይሆናል። አንዱ ላንዱ ይተኩሳል። በስራና በትግላቸው አንድ በተፈጥሮ ግን ሁለት ሆነው፡ አንድም ሁለትም ሆነው ስራቸውን ሰሩ። ያንን ነው የምንፈልገው። አፋርም ስራውን ይስራ። ግንቦት ሰባትም ስራውን ይስራ። ኢህአፓም ስራውን ይስራ። ኦነግም ስራውን ይስራ። ከዚያ ስራው ራሱ የጥምረቱን አስፈላጊነት ያምጣው። ያለበለዚያ እንዴት ነው እዚያና እዚህ የሚረግጡ አላማና ድርጅት ይዘን ህብረት፤ ወይንም ትብብር ወይንም ጥምረት የምንመሰርተው? አይገባኝም።
አልጨረስኩም፤ አስራምናምንኛ ነጥብ አለኝ፤
አሁንም በጣም ይቅርታ እኔ ይሄ ህብረት፣ ጥምረት፣ ትብብር፣ ግንባር፣ ምናምን የሚባል ነገር በጣም የሚቀፈኝ ዋስትናም ስለሌለው ነው። የመጣላትና የመጋጨትም እድሉ ሰፊ ነው። መካሰስ ይኖራል። በተለይ እንደዚህ እንዳሁኑ ሶስት አቅማቸው የተዛባና የማይመጣጠን ሀይሎች ሲጣመሩ፤ የመጣላትና የመካሰስ እድሉ የሰፋ ነው። የአፋር ብድግ ይልና ግንቦት ሰባትን ሊከስ ነው። በስማችን ነገደ፣ ስልጣኑን ሁሉ ያዙት፣ ሳንመካከር ተሰራ፣ የሀብት ክፍፍል ፍትሀዊ አይደለም፣ ግንቦት ሰባት የራሱን ምልመላና ቅስቀሳ ብቻ ያጧጡፋል … በሽ የክስ ዝርዝር ሊመጣ ነው። ሌላኛውም እንደዚያ። የማን ሀብት የማን ሊሆን ነው? ግንቦት ሰባት እንደ ግንቦት ሰባት የለቃቀመውን መዋጮና ሌሎች ቁሶች እንዲሁም የሰው ሀይል ለብቻው ይዞ ሊጓዝ ነው ወይንስ እንዴት ያለ የመከፋፈያ ቀመር ሊፈጥር ነው። ነው ወይስ ትግሉ እዚያ ላይ ሊሆን ነው?
እቺ በጣም ጠቃሚዋ ነጥብ ነች፤
ጥምረት ወይም ትብብር ወይም ህብረት አደጋም አለው። ለነገሩ ጥምረቱ በትግላችን ላይ የሚጨምረው ነገር አለ ብዬ አላምንም። ቢኖርምና በጥምረቱ ድል እያደረግን ብንመጣም እንኩዋን ወያኔ የመጀመሪያው ርምጃው የጥምረቱ አካል የሆኑትን ሀይሎች ማባበልና የሚፈልጉትን ነገር መስጠት ነው። ለምሳሌ ግንቦት ሰባትና ወዳጆቹ ከኦነግና ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ጋር ትብብር ወይንም ህብረት መሰረቱና በትግሉ እየገፉ ወያኔን የሚያሰጉበት ደረጃ ላይ ደረሱ እንበል። የፓርቲ ውህደትና አንድነት እስከሌለ ድረስና ሁሉም ድርጅት እንደ ድርጅት የያዘውን ዓላማ እስካልተወ ድረስ የተሻለ ስጦታ ከሚሰጠው ከማንም ጋር ለመስራት ምንምና ማንም አይከለክለውም። በዚህ ዘመን ለኦነግና ለኦብነግ አላማዎች፤ ከግንቦት ሰባት አይነት የአንድነት ሀይሎች ይልቅ እንደ ኢህአዴግ ያለ የብሄር ድርጅቶች ስብስብ የተሻለ የቀረበ ነው። ኢህአዴግ በብሄሮች መብት እስከ መገንጠል ያምናል። ግንቦት ሰባት በዚህ አያምንም። አከተመ። ግንቦት ሰባትና ኦነግ የሚፈጥሩት ህብረት በባህርዩ በጣም ስስና ዘላቂነቱ የሚያጠራጥር ነው። ስለዚህ እንደ ኦነግ አይነት ሀይሎችን በጥምረቱ ወይንም በትብብሩ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያስገድዳቸው ምክንያትም ግዴታም የለም። ስለዚህ የዓላማ አንድነትና ውህደት ካልሆነ በስተቀር፡ ይሄ ጥምረት ምናምን የሚባል ነገር በመጨረሻ እያወቁ ክስረት ነው። አደገኛ ነው። ተክሌ ምን አለ ትላላችሁ አይሰራም። በሰራና እኔ ባፈርኩ።
ጎበዝ - እንደማጠቃለያ
ወያኔ በጥምረት አይደለም ያሸነፈን። ወያኔ ከድርጅታዊ ጥምረት ወይንም ከድርጅታዊ ግንባር ይልቅ በድርጅታዊ ጥበትና ሞኖፖሊ ነው ያሸነፈን። ሕወሀት እንደ ትግሬ ተደራጅቶ፡ እንደአማራ ጠላት ተሰብስቦ እንደ ትግሬ ጦር ተዋግቶ ነው ያሸነፈን (የትግራይ ህዝብ ለዚህ ተጠያቂ አይደለም)። እንደ ኢትዮጵያዊ ሀይል አይደለም ያሸነፈን። እንደ ሕወሀት መደራጀታቸው ረዳቸውና አሸነፉን። በመጨረሻ አካባቢ እስካሁንም ድረስ እን አባዱላ ገመዳንና እነ ታምራት ላይኔን ለቃቅመው እንደ ኢህአዴግ መደራጀታቸው ከትግሉ ይልቅ ቀጣዩን የመንግስትነት ጉዞ ለመጓዝ ነው የረዳቸው። እንጂ እንደ ህወሀት ነው ያሸነፉን። ካሸነፉን ደግሞ ካሸናፊዎች መማር አለብን። ከጠላትም ቢሆን። በወያኔ የትግል ታሪክ ውስጥ የስራ ጥምረትና ሕብረት እንጂ የነበረው የፖለቲካ ፕሮግራም ሕብረት አልነበረም። ጥንትም ሕወሀት ናቸው፡ አሁንም ሕወሀት ናቸው።
ከዚያ በተረፈ
እድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ከፖለቲካ የተማርነው ነገር በምንም መልኩ አለመተማመንን ነው። ወይንም ፖለቲከኞች ቃላቸውን ይጠብቃሉ ወይንም እንደኛ ያስባሉ ወይንም ቅን ልቡና አላቸው ተብሎ ብቻ በማመን የሚሰራ ስራ አለመኖሩን ነው። ስለዚህ ገና ለገና ወደ ጥምረት የሚመጡ ድርጅቶች ሁሉ ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ የአገርን ፍላጎት ያስቀድማሉ ብሎ ማሰብ የዋህነትና ስህተት እንደሆነ ስምም ድርጅትም ሳንጠራ በዚህ አምስት አመታት ውስጥ እንኩዋን ያየነው ይበቃል። በመሰረቱ አንድ ድርጅት ከሌላኛው ድርጅት ጋር መዋሀድ እየቻለ አላማዬንና ፕሮግራሜን ጥዬ አልዋሀድም፤ ነገር ግን በአነስተኛ ፕሮግራም ለተወሰነ ግብ ልጣመር እችላለሁ ብሎ ወደ ጥምረት ሲመጣ ከተቃራኒ ሀይል ለምሳሌ ከኢህአዴግ በፕሮግራሙ ላይ የሰፈረውን አላማ ሊያሳካ የሚችል የተሻለ እድል ከተሰጠው ጥምረቱን ጥሎ ወደዚያ የማይሄድበት ምክንያት የለም። ስለዚህ የመተማመን ጥምረት አይሰራም። ይሄ ስለግለሰቦች አይደለም። ይሄ ስለብርሀኑና ነአምን ዘለቀ አይደለም። ስለግለሰቦችም ቢሆን ሀይሉ ሻውልንና ልደቱ አያሌውን አይተናል። ግዛቸው ሽፈራውንና መስፍ ወልደማርአምን አይተናል። ነአምን ዘለቀ ወይንም ዶ/ር ብርሀኑ የሆነ ነገር አድርገው ጥምረቱን ያፈርሱታል አይደለም ስጋቴ። ቀድሞውንስ ነገር ነአምንና ብርሀኑ ውህደት እንጂ ጥምረት ውስጥ ምን ዘፈቃቸው? ከሆነ ይቅናችሁ ግን አይመስለኝም። ጥምረት አይደለም የሚያስፈልገን፡ ውህደት ነው። ከዚያ ትንሽ ድፍረት።
--------------------------------------------------------------------------------
ልጅ ተክሌ ቫንኩቨር፡ ካናዳ፡ ነሀሴ 2002/2010
[1] http://timret.org/documents/press_release_Timiret_Formation_amh.pdf እና http://timret.org/documents/alliance_amh.pdf የጥምረቱን አላማ እዚህ ላይ ያገኙታል።
[2] http://www.ginbot7.org/amh_wp/?p=762
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment