Wednesday, December 23, 2009

አኬልዳማ

በአገሬ ሕዝብ ላይ- ሰቆቃ
ምነው አልቆም አለ-አላበቃ
ርህራሄ ተነፍጎት-
እየኖረ በዋይታ
ስው ባምሳያው- ሰብዓዊነት
አልሰማው ብሎ-ኃላፊነት
ሰብዓዊ መብቱ- ተረግጦ
ወገን በወገን ላይ-ዶልቶ
ወገን ሞቶ-ወገን ገድሎ
በፉከራ
ፈጣሪም ሳይፈራ
ዘራፍ ብለን ራሳችን- በራሳችን
እኛው በእኛ ላይ- አምፀን
ጳጳስ ገድለን- ጳጳስ ሾመን
አሃዱ ብለን በስልሳ ራስ- አንገት ቀልተን
የኛን ራስ- እኛው ጠልተን
የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ -ገና ጨቅላ
የአስር ዓመት ልጃገረድ- እምቦቅላ
ሽኘን በሞት- በሽለላ
ገዳይ ብለን በፉከራ።

ድንበር ሰርተን- ሸሁን ገፍተን- ካህን ጠልተን
በማናውቀው ርዕዮተዓለም- ተጠምቀን
ሽብር ሆኖ ቀይና ነጭ-ወገን ከፍሎ
አንዱ ሌላውን-ሊያጠፋ ተገዝቶ ምሎ
ልንጠፋፋ-ተገዳድረን
በጥፋት ካህን ፊት-ምለን ተገዝተን
ላንተኛ- በሃሳብ የተለየን ወንድማችን
አፈር ሳይሆን

እናት አሳዝነን- ለአባት ማቅ አልብሰን
እርር አርገን
ልጆች ከጉያ- ተነጥቀው
ለመቃብር -ተዳርገው
ዋይታ በዝቶ- ለቅሶ ቢሆን
ዘፈን ጠፍቶ -ሳቃችን ሆኖ ሃዘን
ሺህዎች -እንደቅጠል ቢረግፉ
ቢበዛብን -የእኛው በእኛ- ፍጡር ግፉ
አኬልዳማ ሆነ ቃሉ- አኬልዳማ
የሞት ጥላ አጥልቶብን-የእልቂታችን ካራማ።

እኛው በእኛ ላይ- ከፍተን
እንደ ወንድማማች- በሰላም አብረን
መኖር ተሳነንና-ቀጠለ ጥፋታችን።
ዛሬም እንደትናንቱ- በሃሳብ ለተለየን
ይሙት በቃ- ብለን በየን
እንደ ፋንታ በላይ- ሁሉ
ይሙት አልን ሙሉነህ- ይሙት አልን ብርሃኑ
እንደ መርዕድ እና አመሃ- ደምሴና ቁምላቸው
ፈረድን-
ይሙት በቃ በመስፍን
በመላኩና በአንዳርጋቸው።

መደብን ከመደብ- ጎሣን ከጎሣ ሆነ ብለን
ኃይማኖትን ከኃይማኖት- በማጋጨት ተክነን
ከጎሰኝነት ከሃይማኖት ከመደብ ወገንተኝት
መጽዳት አቅቶን
በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር -ማረፍ ወንጀል ሆኖ
ደም ይፈሳል ጅረት ሆኖ- ቱግ ብሎ
የጥቂቶች ፍልጎት- በአብዛኞቻችን ጀርባ ተጭኖ
አሜን ብለን እንድንኖር- ህግ ህኖ
መልካም ስራ ተንቆ
ወንጀል በተገላቢጦሽ
መልካም ተብሎ
የምንኖርባት ምድር- ሆናለች አኬልዳማ
የሞት ጥላ ያጠለባት- የጥላቻ ካራማ

ልዩነታችን የሚፈታው- ሆነና በጠመንጃ
ገዥ ሆኖ አፈሙዝ- ግኡዝ ፍጡሩ ሳንጃ
የትኛው ጅኒ- አጋንንት ቢያርፍብን ነው
ምድራችን ለዓመታት- አኬልዳማ የሆነው?
መቸ ይሆን የሚቆመው
እኛው በእኛ ላይ የፈጠርነው
መከራው?

ዳግማዊ ዳዊት
ታህሳስ 2002 ዓ.ም.
Ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: